ወጣቶች ልማትን ማሳለጥ እና ሰላምን ማስፈን ይጠበቅባቸዋል።

6

ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በምኒልክ ክፍለ ከተማ ባቄሎ ቀበሌ ለሚገኙ ለ775 ወጣቶች በልዩ ኹኔታ 200 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጣቸው መደረጉን የከተማ አሥተዳደሩ መሬት መምሪያ ኀላፊ እታለማሁ ይምታቱ ተናግረዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ የገጠር ማዕከል ለመመስረት እየተሠራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኀላፊዋ ከመኖሪያ ቤት ማኅበር አሠራር በተለየ ኹኔታ ወጣቶችን በ34 ብሎክ በማደራጀት የመሥሪያ ቦታ መሰጠቱን አንስተዋል።

የወል መሬት ባለመኖሩ ምክንያት ወጣቶች ለአርሶ አደሮች ካሳ እንዲከፍሉ መደረጉን ጠቅሰዋል።

መምሪያው በፕላኑ መሰረት እንዲመራ በማድረግ የካሳ ግምት በመሥራት እና ለአርሶ አደሮች ካሳው ፈጥኖ እንዲደርስ የማድረግ ሥራ ማከናወኑንም ገልጸዋል። ለዚህም የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎችም የጎላ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ከተማ አሥተዳደሩ ለወጣቶች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ መስጠቱ የሕዝቡን ጥያቄ የመመለስ አንዱ አካል ነው ብለዋል።

ይህም የባቄሎ ቀበሌን በከተማ ፕላን መሰረት በአግባቡ እንዲመራ የሚያደርግ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ወጣቶች የተረከቡት ቦታ የገጠር ኮሪደር ልማት አሠራር መሰረት በማድረግ ግንባታ የሚደረግበት መኾኑን ተናግረዋል።

ለሌሎች አካባቢዎች ተምሳሌት እንዲኾን በማድረግ ሂደት ከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

መንግሥት የወጣቶችን ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገ ሁሉ ወጣቶችም ልማትን በማሳለጥ እና ሰላምን በማስፈን ሚናቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቦታ የደረሳቸው ወጣቶችም የረጅም ጊዜ ጥያቄያቸው በመመለሱ እንደተደሰቱ ተናግረዋል። ከተማ አሥተዳደሩ ላደረገላቸው ትብብርም ምስጋና አቅርበዋል።

ወደ ፊትም በከተማው ለሚከናወኑ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleንጋት ሐይቅ በርካታ ጸጋዎችን የያዘ ነው።
Next articleሰላምን አጠናክሮ ማስቀጠል ተማሪዎች ያለችግር ተምረው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል።