
አዲስ አበባ: ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ንጋት ሐይቅን በተመለከተ ለቀጣይ 15 ዓመታት የሚያገለግል ማስተር ፕላንን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በርካታ ሃብቶች ያሉት ነው። ንጋት ሐይቅን የመሰለ ግዙ ሐይቅ የፈጠረ የሀገር ፀጋ ነው። በቀጣይ ሐይቁን ተከትሎ የሚፈጠሩ ከተሞች፣ የሆቴል ቱሪዝሞች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንደሚኖሩት ይጠበቃል።
የሐይቁን ደኅንነት በማስጠበቅ ይዞት የሚመጣውን ትሩፋት በአግባቡ ለማሥተዳደር አግባብ ያለው የማስተር ፕላን አስፈልጓል።
የውኃ እና ኢነርጅ ሚኒስትር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) ለቀደሙ ነገሥታት እና ትውልዶች ዓባይ የዘመናት ቁጭታቸው እንደነበር ገልጸዋል።
ይህ እንዳይሳካ ታሪካዊ ጠላቶች ጥረት አድርገው ቁጭቱ ለዚህ ትውልድ ተሻግሯል ብለዋል። ይህ ትውልድ እና መንግሥት ግን ጫናዎችን ሁሉ ተቋቁሞ በይቻላል መንፈስ ለራሱም ኾነ ለቀጣዩ ለትውልድ ኩራት የኾነ ታሪካዊ ሥራን በሕዳሴው ግድብ አሳክቷል ብለዋል።
የሕዳሴ ግድቡ እና ንጋት ሐይቅ የሚሰጠውን ግልጋሎት ዘላቂ ለማድረግ ከደለል ተጠብቆ እና ከአካባቢ ብክለት ድኖ እንዲቀጥል ማስተር ፕላኑ አስፈልጓል ነው ያሉት።
ለትራንስፖርት፣ ለቱሪዝም እና ለዓሳ ሃብት አቅም እንዳለውም ገልጸዋል።
ማስተር ፕላኑ ለእኛ ብቻ ሳይኾን የታችኛውን የተፋሰስ ሀገራትም የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ የተዘጋጀ ነው ነው ብለዋል።
ይህ ማስተር ፕላን ሁላችንም ባለድርሻ አካላት ድርሻችን አውቀን እንድንሠራ እና በቅንጅት ተግባራዊ እንድናደርገው ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የዚህ ማስተር ፕላን ትግበራ ቀጣይ ሀገሪቱ በውኃ ልማት ዘርፍ ለምትሠራቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች መነሻ ኾና ያገለግላልም ብለዋል።
በመድረኩ ላይ በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።
በቀረቡ ጽሑፎች እና በማስተር ፕላኑ ላይ በመድረኩ ተሳታፊዎች ውይይቶች ተካሂደውባቸዋል።
በማስተር ፕላኑ ላይ ተከታታይ ውይይቶች ተደርገው ሁሉን የሚያስማማ እና ለዘላቂ ልማት የሚበጅ ውሳኔ ተላልፎ ፕላኑ እንደሚጸድቅም ይጠበቃል።
ዘጋቢ:- አዲሱ ዳዊት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!