
አዲስ አበባ: ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የንግድ ትርኢት እና ጉባኤ አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል።
ከጥቅምት 20 እስከ 22 2018 ዓ.ም በሚካሄደው የንግድ ትርኢት 14ኛው የኢትዮ ፖልተሪ ኤክስፖ(ኢትዮፔክስ)፣ 10ኛው የአፍሪካ እንስሳት አውደ ርእይ (አሌክ)፣ 5ኛው የአፒካልቸር እና አኳካልቸር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት እና ዘንድሮ ለ2ኛ ጊዜ የሚካሄደው የባዮ ኢነርጂ የንግድ ትርኢትን ጨምሮ ጥራት ያላቸው የዘርፉ አንቀሳቃሾችን የሚያሳትፍ ይኾናል ተብሏል።
ሁሉን አቀፍ የእንስሳት ርባታ ቴክኖሎጂ ግብአት እና መፍትሔዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በሚዘጋጀው ኹነት የእንስሳት ሀብት ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን ለማስተዋወቅ እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑም ተገልጿል።
ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት አውደ ርእይ እና ጉባኤዎች በዶሮ፣ እንቁላል፣ በወተት እና ስጋ ዘርፎች እድገት እና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የፕራና ኢቨንትስ ሥራ አስኪያጅ ሜሮን ሰለሞን ገልጸዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዳይሬክተር ዓለማየሁ መኮንን (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ቀዳሚ ሀገር ብትኾንም የወተት ምርቶችን ጨምሮ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባቸው የእንስሳት ተዋፅዖ ምርቶች ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጓት ነው ብለዋል። የተትረፈረፈ ምርትን በማምረትም ይሄንን ማስቀረት ላይ በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ሁነቱም ለዚህ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ለሦሥት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ሁነት ላይ ኢትዮጵያን እና ኔዘርላንድን ጨምሮ ከ14 ሀገራት የተውጣጡ ከ80 በላይ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተዋናዮች ይሳተፉበታል። ከ5 ሺህ በላይ የምሥራቅ አፍሪካ አና ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች በንግድ ትርኢቱ ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!