
ደሴ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከ13 ሄክታር መሬት በላይ የሚኾን መሬትን በስንዴ፣ በጤፍ እና በማሽላ ያለሙ የሴፍትኔት ልማት ተጠቃሚዎች የራሳቸውን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ በአካባቢው ላይ ለውጥ እያመጡ እንደኾነ ገልጸዋል።
በሥራው ላይ የተሰማሩ ዜጎች በምግብ ሰብል እራሳቸውን ከመቻል ባለፈ የሚያመርቱትን ምርት ለገበያ እያቀረቡም ይገኛሉ።
በመርሐግብሩ የታቀፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከተረጅነት በመላቀቅ በራሳቸው ሠርተው በመለወጥ የተሻለ ገቢ እየፈጠሩ እንደኾነም ተናግረዋል።
በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የምግብ ዋስትና እና ሴፍትኔት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እታፈራሁ አሰግደው በዚህ መርሐግብር በአካባቢ ልማት እና በቀጥታ ድጋፍ 12 ሺህ 291 ዜጎች ተጠቃሚ ኾነዋል ብለዋል።
በተለይ 2ሺህ 400 የሚኾኑት ዜጎች በከተማ ግብር እና የተለያዩ ሰብሎች እና የጓሮ አትክልቶች ልማት ላይ ተሰማርተው ከራሳቸው አልፈው የከተማውን ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንደሰን ልሳነወርቅ ከተማ አሥተዳደሩ በአካባቢው ልማት ለሚሳተፉ የመርሐግብሩ ተጠቃሚዎች ከዚህ ቀደም ጥቅም የማይሰጡ ቦታዎችን በማመቻቸት ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል ነው ያሉት።
በዚህም ከዚህ በፊት ከተማ ላይ ይሠራሉ ተብሎ የማይታሰቡ የግብርና ሥራዎች በመሠራታቸው በሰብል ምርት የተሻለ ውጤት እየታየ እንደኾነ አብራርተዋል።
የልማታዊ ሴፍቲኔት ውጤታማ ሥራዎችን ለማስፋት ከተማ አሥተዳደሩ በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን አምባቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!