
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በስጋ እና ወተት ምርት ላይ መሻሻሎችን ለማምጣት የዝርያ ማሻሻል ሥራዎች ወሳኝ እንደኾኑ በእንሰሳት ሃብት ልማት ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የዝርያ ማሻሻያ ከአደኛው ዝርያ ላይ ያለውን የተሻለ ነገር ወደ ሌላኛው እንዲሸጋገር እና ጥሩ ውጤት ለማምጣት የሚደረግ የምርምር ሥራ ነው።
የምርምር ሥራ ሢሠራ የውጭ ዝርያዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ የሀገር ውስጥ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ማድረግ የበለጠ ውጤታማ መኾን እንደሚያስችል ይነገራል።
ብዙ ጊዜ የእንሰሳት ዝርያ ማሻሻል ሲነሳ ትኩረት የሚደረገው ከሀገር ውስጥ ዝርያዎች ይልቅ ከውጭ የሚመጡ ዝርያዎች ላይ ሲኾን ይስተዋላል። ነገር ግን በምርምር ቢደገፉ የተሻለ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ የሀገር ውስጥ ሀብቶችም አሉ። ከእነዚህ መካከል የፎገራ ዳልጋ ከብቶች እየተባሉ የሚጠሩት ዝርያዎች ይጠቀሳሉ።
የፎገራ ዳልጋ ከብቶች በረግረጋማ እና ውኃ ከሚበዛበት አካባቢ የሚኖሩ ናቸው። እነዚህ ከብቶች የተሻለ ምርት የሚሰጡ ናቸው። በፎገራ ወረዳ ወጅ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ አዲስ እሸቱ የፎገራ ዳልጋ ከብቶች አርብቶ አደር ናቸው፡፡
አቶ አዲስ እሸቱ ወደ ትዳር ሲገቡ እሳቸውም ኾነ የትዳር አጋራቸው በቂ የእርሻ መሬት ባለመኖራቸው ሁለት የፎገራ የወተት ላሞችን በመግዛት ማርባት እንደጀመሩ ይገልጻሉ፡፡
አቶ አዲስ እሸቱ የእርባታ ሥራዎችን ከወረዳው የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ጋር በመቀናጀት በፎገራ ኮርማ በማዳቀል ቁጥራቸው ከፍ እንዲል መሥራታቸውን ነው የገለጹት። በተሠራው ሥራም የከብቶቹ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ወተታቸውንም በመሸጥ ተጠቃሚ መኾን እንደቻሉም አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም ከአንድ ላም በቀን ሁለት ጊዜ በማለብ ከ10 እስከ 12 ሊትር ወተት ማግኘት እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡ ይህም ከራሳቸው አልፎ ለኪራይ የሚኾኑ ቤቶችን በመሥራት እና ልጆቻቸውን አስተምረው ጥሪት እንዲይዙ እንደረዳቸው ተናግረዋል።
ሌላኛው በፎገራ ወረዳ ዋገጠራ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት ጥሩሰው ዓለሙ የፎገራ የዳልጋ ከብቶች ዝርያ በወተትም ኾነ በስጋ ጥሩ ምርት የሚያስገኙ እንደኾኑ ወላጆቻቸው ሲያወሩ ይሰሙ እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡
ዝርያው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መሄዱን እና ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ዝርያውን ለማስፋፋት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በዚህም ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ አራት የፎገራ ዳልጋ ከብት አውራዎችን ከግብርና ጽሕፈት ቤቱ በመውሰድ ለስጋ የማድለብ ሥራ መጀመራቸውን አስታውሰዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከፎገራ ላሞች ጋር በማዳቀል የወተት እና የስጋ ከብቶችን በማሳደግ ተጠቃሚ እንደኾኑም ነው የጠቆሙት፡፡
በዚህም ከወተት ላም በቀን ከስምንት እስከ 10 ሊትር ወተት በማለብ የወተትም ኾነ የቅቤ ተጠቃሚ መኾን እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።
የተሻሉ የዝርያ ከብቶችን በማድለብም እስከ 90 ሺህ ብር ድረስ በመሸጥ ተጠቃሚ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ይህም ኑሮአቸውን በቀላሉ ለመለወጥ እንዳበቃቸው ነው የተናገሩት፡፡
ለዚህ ደግሞ የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ባለሙያዎች የፎገራ የዳልጋ ከብት ዝርያዎች ውጤታማ እንዲኾኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ እያገዙአቸው መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት መምሪያ የእንስሳት የእርባታ ባለሙያ ገነት ጥላሁን የፎገራ ዳልጋ ከብት ዝርያዎችን ለማባዛት በጣና ኮሪደር ሊቦ፣ ፎገራ እና ደራ ወረዳዎች ላይ በስፋት እየተሠራባቸው ነው ብለዋል፡፡
በእነዚህ ወረዳዎች ያሉ የፎገራ ዳልጋ ከብቶችን ንጹሕ ዝርያ እንዳለ ለማስጠበቅ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
እነዚህ ዝርያዎችን ለማባዛት እና ንጹሕ ዝርያዎችን ለማስቀጠል በቻግኒ ከተማ የፎገራ ዝርያ የዳልጋ ከብት ማቆያ ማዕከል ኮርማዎችን በማስመጣት በጣና ኮሪደር ላሉ ወረዳዎች በማሰራጨት ከንጹሕ የፎገራ ላም እና ጊደሮች ላይ እንዲዳቀሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
አንድን እንስሳ ዝርያውን ማቆየት ወይም ዝርያውን ማራባት ብቻ አይደለም ምርታማ የሚያደርገው ያሉት ባለሙያዋ በዋናነት የሚመገቡት መኖ እና የጤና አጠባበቃቸው መታየት እንዳለበትም ገልጸዋል።
እነዚህ ባልተሟሉበት እና የአርሶ አደሮች ግንዛቤ ባልተሻሻለበት አካባቢ እነዚህ የተሻሻሉ የፎገራ ዳልጋ ዝርያዎች እንደሌሎቹ የአካባቢ ዝርያዎች ምርታቸው ተሻሽሏል የሚባልበት ደረጃ ላይ አለመድረሳቸውንም አስገንዝበዋል።
ንጹሕ የኾኑ የፎገራ ዳልጋ ከብት ዝርያዎችን የተሻለ ሊመግቡና ሊንከባከቡ ለሚችሉ አርሶ አደሮች በመስጠት ክትትል እና ድጋፍ በማድረግም ዝርያውን ለማቆየት እና ለማስቀጠል ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡
አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ይዘቱን ያልለቀቀ የተሻሻለ መኖ እና የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርትን እንዲጠቀሙ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት። ማሳን ሳይጎዱ ለእንስሳት የተሻለ ንጥረ ነገር ይዘት ያላቸውን መኖዎች በማምረት እንዲጠቀሙ በማድረግ ከብቶቻቸውን እንዲቀልቡ እና እንዲንከባከቡ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በተሠራው ሥራ የተገኘውን ውጤት እያዩ የአካባቢው አርሶ አደሮች የፎገራ ዳልጋ ከብትን የማርባት እና የማድለብ ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱንም አስገንዝበዋል፡፡
የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ቢሮ የእንስሳት እርባታ ተዋጽኦ እና መኖ ልማት ዳይሬክተር መኳንንት ዳምጤ የፎገራ ዳልጋ ከብት ዝርያ ያላቸውን ጠቀሜታ በመለየት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዝርያቸው የተሻለ ውጤት የሚሰጥ በክልሉ ከሚገኙ ምርጥ እና በጣም ጥሩ ከሚባሉ ዝርያዎች መካከል ናቸው ነው ያሉት።
ዝርያው ከሌሎች ዝርያዎች ጋር እየተዳቀለ የመኖር ሕልውናውቸው አደጋ ላይ ወድቆ መቆየቱን ተናግረዋል። ይህ ዝርያ ጨርሶ እንዳይጠፋ የቻግኒ ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል በማቋቋም ንጹሕ የፎገራ ወይፈኖችን በማባዛት የፎገራ ዝርያ በሚገኝባቸው ቀበሌዎች እና ወረዳዎች በማሰራጨት ዝርያውን ወደ ነበረበት ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በማዕከሉም 1ሺህ 218 የሚደርሱ ንጹሕ የፎገራ ዝርያዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። በእነዚህ የፎገራ ከብቶች ዝርያው እንዳይጠፋ የመጠበቅ ሥራ ይሠራልም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በባሕር ዳር በሚገኘው የእንስሳት ማሻሻያ ማዕከል እና በአንዳሳ የእንስሳት ምርምር ማዕከል የፎገራ ኮርማዎች አባላዘር በማምረት በላብራቶሪ በማሳደግ በአዳቃይ ባለሙያዎች አማካኝነት የማዳቀል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ለአርብቶ አደሮችም በ5 ዓመታት ውስጥ 635 የሚኾኑ ንጹሕ የፎገራ ኮርማዎችን ንጹሕ የፎገራ ዝርያዎች ባሉባቸው በጣና ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ማሰራጨታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም የፎገራ ዝርያ እንዳይበረዝ፣ እንዳይከለስ ተበርዞም ከኾነ ወደነበረበት እንዲመለስ የደም መጠናቸው ከፍ እንዲል የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መንገድ ዝርያው ለመጥፋት ስጋት ኾኖ የነበረው በቁጥርም በጥራትም ወደ ነበረበት እንዲመለስ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በዚህም ሊጠፋ ከነበረበት ወደ ተሻለ መንገድ መምጣቱን እና ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!