
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሺህ ዓመታት የቀይ ባሕር ገናና ባለቤት እንደነበረች የሚወሳላት ኢትዮጵያ የነበራትን የባሕር በር በታሪክ አጋጣሚ አጥታለች።
ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ በዘላቂነት የራሴ የምትለው የባሕር በር አጥታ ወደ ጎረቤቶቿ እንድታማትር ስትገደድ ይስተዋላል። ሀገሪቱ እያነሳችው ያለው የባሕር በር የጋራ ተጠቃሚነት ጥያቄ ፍትሐዊ እና መርሕን የተከተለ ሐቅ ነውም ይሉታል።
አለማየሁ እርቂሁን (ዶ.ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላም እና ጥናት ተቋም ውስጥ ተመራማሪ ናቸው።
የባሕር በር ከሌሎች ዓለማት ጋር መገናኛ መስመር ነው ይላሉ። ይህም ከሌሎች የመገናኛ መንገዶች ማለትም ከአየር እና ከየብስ የመገናኛ መንገዶች የተሻለ ርካሽ እና አዋጩ መንገድ እንደኾነ ገልጸዋል።
ሀገራት ያላቸውን ለሌሎች የሚልኩበት እና የሌላቸውን ደግሞ ከሌሎች የሚያስገቡበት የመለዋወጫ በር እንደኾነም ነው የተናገሩት። የባሕር በር ባለቤት መኾን የሚቻልባቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መቀመጣቸውን ዶክተር አለማየሁ አመላክተዋል።
ከእነዚያም ውስጥ የሀገራቱ የትላንት ታሪካዊ ይዘት አንዱ እንደኾነ አንስተዋል። ትናንት የነበረው ከባሕር በር ጋር የተያያዘ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት ለባሕር በር ባለቤትነት መነሻ ነጥቦች እንደሚኾኑ ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ በታሪክ ለረጅም ዘመናት የቀይ ባሕር ባለቤት ኾና የቆየች ታሪካዊ ሀገር ናት ይላሉ ዶክተሩ። ከዘመነ አክሱም ጀምሮ ቀይ ባሕርን ታሥተዳድር እንደነበር ታሪክ ላይፋቅ ከትቦታል ነው ያሉት።
በቀይ ባሕር ላይ ባለቤት መኾን ብቻም ሳይኾን የበላይ እና ኃያል ሀገር የነበረች ናት ብለዋል። የታሪክ ባለቤትነቷም ባንድ ጊዜ ታይቶ የጠፋ ሳይኾን ዘመንን የተሻገረ ታሪክ ነው ያላት ይላሉ።
ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን በማሥተዳደር እና ባለቤት በመኾን ዘመን የተሻገረች የባሕር በር ባለቤት ሀገር መኾኗን ነው የገለጹት ዶክተር አለማየሁ። ሌላው ለሀገራት የባሕር በር ባለቤትነት እንደመነሻ የሚታየው ቅርበት ነው ብለዋል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ አሁን ባለው አቀማመጧ እንኳ ቢታይ ከአሰብ 60 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቃ ትገኛለች ብለዋል።
ይህ ኾኖ እያለ ሌሎች አውሮፖውያን ሀገሮች ቀይ ባሕር ላይ መጥተው ወታደራዊ ቤዛቸውን ሲመሠርቱ ፍትሕ የተነፈጋት ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ መቀመጫ የላትም ነው ያሉት።
የራሷ ከነበረው ቀይ ባሕር ላይ ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊም ኾነ ሌላ ጥቅም እንዳታገኝ ተደርጓል ብለዋል። “ኢትዮጵያ ኾን ተብሎ በር ተዘግቶባታል” ነው ያሉት።
ይሁንና ይላሉ ዶክተሩ ሀገሪቱ እውነታን መሠረት አድርጋ ከተነሳች የባሕር በር የማታገኝበት ምንም አይነት ምክንያት የለም ብለዋል። በሕዝብ ቁጥር ብዛት ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካ ሀገራት የምትሰለፈው ሀገር ጥያቄውን የማንሳቷ ነገር አማራጭ የሌለው እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያውያን የሚያነሱት ጥያቄ የቅንጦት ሳይኾን የህልውና ጉዳይ መኾኑንም ማጤን ተገቢ እንደኾነ ነው የገለጹት። የኢትዮጵያውያን ህልውና የሚረጋገጠው ደግሞ የባሕር በር ባለቤት መኾን ሲቻል እንደኾነም ገልጸዋል።
ዓለም ፍትሐዊ ትሁን ከተባለ ኢትዮጵያ በታሪካዊ ስህተት ያጣችው ይዞታዋ ሊመለስላት ይገባል ነው ያሉት። “ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ቀይ ባሕርን ያጡት ባልመከሩበት ነው” ብለዋል ዶክተር አለማየሁ።
ሕዝቡ ሳይመክርበት እና ሳያምንበት ቀይ ባሕር መውጣቱን ነው ያነሱት። በፓርላማ ሳይወሰን፤ የሕዝቦች ይሁንታ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ በታሪካዊ ስህተት ያጣነው ሃብታችን እንደኾነ ነው የገለጹት።
አሁን ኢትዮጵያ እያነሳችው ያለው ጥያቄ ግልጽ እና ውኃ የሚያነሳ በመኾኑ የባሕር በር የማግኘት ዕድሏ አያጠራጥርም ብለዋል።
ቀይ ባሕር እና አካባቢው የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት የሚበዛበት በመኾኑ የፖለቲካ ትኩሳት ይበዛበታል ነው ያሉት። እናም ሀገሪቱ ለቀጣይ ደህንነቷም ሲባል የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋ ወቅታዊ እና መሠረታዊ ነው ብለዋል።
በተሳሳተ ትርክት የቀይ ባሕርን ታሪክ ማንሳት እንደ ትልቅ ስህተት ሲቆጠር ቆይቷል የሚሉት የታሪክ ምሁሩ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ እና እንደተመራማሪ ጥያቄውን አጥብቄ እደግፋለሁ ነው ያሉት።
ጥያቄው ዛሬ ባይነሳ እንኳ ታሪኩን የሚመረምር የቀጣይ ትውልድም ሊያነሳው የሚችል ፍትሐዊ ጥያቄ ነው ብለዋል። ትናንት የተፈጠረችው ኤርትራ የባሕር በሩ ባለቤት እኔ ነኝ ካለች እንኳ ታሪክን መካድ ነው ይላሉ።
ትናንት የታሪክ ተወቃሾች ያሳለፉትን አንጡራ ሃብት የዛሬ ትውልዶች እንዴት ብለን ማንሳት ትክክል ነው ብለዋል። የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ይህ ሲኾን ግን ኢትዮጵያ ሃሳቡን በሠለጠነ መንገድ በማቅረብ እና የአዋጭነት ስሌትን አንግባ መኾን እንዳለበት ምክረ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
የውስጥ አንድነት እና የዲፕሎማሲያዊ ብስለት እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!