
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ዓላማ የሰው ልጅ ማንበብ፣ መጻፍ እና ስሌትን መማር እንዲችል ከማድረግ ባለፈ የተሻለ ማኅበረሰብ ብሎም ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ነው።
ይህ እንዲኾን ደግሞ በትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ማረጋገጥ ላይ መንግሥት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ባለፈ ጠንካራ የሕዝብ ተሳትፎ የማይተካ ሚና አለው።
በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር። ለዚህ ደግሞ ፕሮፌሰር አዱኛው ወርቁ በደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ወረዳ ያከናወኗቸው ሥራዎችን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል።
ፕሮፌሰሩ ካከናወኗቸው ሥራዎች ውክጥ በእብናት ወረዳ የገላ መታጠቢያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ይገኝበታል።
የፕሮፌሰር አዱኛው ወርቁ ተወካይ ማራቸው ሙጬ እንዳሉት ትምህርት ቤቱ 16 የመማሪያ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ሦስት ቤተ ሙከራዎች፣ መጽሐፍት የተሟሉለት ቤተ መጽሐፍት፣ 30 ኮምፒውተሮችንም የያዘ የአይሲቲ ክፍል እና 13 ክፍሎች ያሉት የአሥተዳደር ቢሮዎችን የያዘ ነው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የመምህራን የትምህርት አይነቶች፣ እያንዳንዱ ክፍል ሁለት መምህራንን የሚይዝ 20 ክፍሎች ያሉት እና 180 የሚኾኑ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የሚኾን መጠለያ እንደያዘም ነው ተወካዩ የገለጹት።
በእብናት ከተማም በሚገኘው ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅም ሁለት ብሎኮችን አስገንብተዋል። ለተማሪዎች ማሠልጠኛ የሚያገለግሉ 75 ኮምፒውተሮችን ለኮሌጁ ድጋፍ እንዳደረጉም ነው የገለጹት። “አምቦ በር” እየተባለ በሚጠራው አካባቢም መማሪያ ክፍሎችን ገንብተዋል ብለዋል።
ከትምህርት ባለፈ ማኅበረሰቡ በቅርበት የሚገለገልበት 22 ወፍጮዎችን በተለያዩ ቀበሌዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተደራሽ አድርገዋል ነው ያሉት። ከወፍጮዎች የሚገኘው ገቢ በምጣኔ ሃብት ዝቅተኛ ለኾኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማሟያ እንዲውል አድርገዋል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ የንጹሕ መጠጥ ውኃም ለማኅበረሰቡ እንዳስገነቡ ገልጸዋል።
ፕሮፌሰሩ እነዚህን እና መሰል ሥራዎችን ቢሠሩም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከሰተው ግጭት የትምህርት ቤቶቹ የሃብት ዝርፊያ እንዳጋጠማቸው ነው ተወካዩ የነገሩን። ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው መቆየታቸውንም ገልጸውልናል። አሁን ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በተሠራ ተግባር ተማሪዎች ተመዝግበው እየተማሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ተማሪዎች የተሟላ ትምህርት እንዲያገኙ
ማኅበረሰቡ ጉዳት የደረሰባቸውን እና የተዘረፉ ንብረቶችን ሊያሟላ ይገባል ብለዋል። የትምህርት ተቋማት ጤናማ የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዲያስቀጥሉ ማንኛውም አካል የትምህርት ተቋማትን ለፖለቲካዊ አላማ ማራመጃነት ከማድረግ ሊቆጠብ ይገባል ብለዋል።
ጉዳት እንዳይደርስባቸውም ኀላፊነት ወስዶ እንዲሠራም ጠይቀዋል። ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ “ማኅበረሰቡ ትምህርት ቤቶችን መጠበቅ፣ በሃብት ማጠናከር እና ማልማት ይገባዋል” ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ በአማራ ክልል የመማር ማስተማር ሂደቱ በተለያዩ ችግሮች ሲፈተን መቆየቱን ገልጸዋል። በ2018 ዓ.ም ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮች እንዳይደገሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጎዱ ምህርት ቤቶችን የመጠገን ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎችም የትምህርት ቁሳቁስ ከማኅበረሰቡ የማሰባሰብ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል። መምህራንም ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ነው የገለጹት።
አሁን ላይም ያልተመዘገቡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የትምህርት ባለሙያዎችን ከተለያዩ አደረጃጀቶች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በማቀናጀት ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
ትምህርት ቢሮም የተለያዩ መጽሐፍትን የማሟላት ሥራውን እየሠራ ነው ብለዋል ። በክልሉ የሚገኙ “ተማሪዎች በጊዜያቸው ማግኘት የሚገባቸውን ትምህርት እንዲያገኙ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም” አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!