
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬ ባካሄደው 49ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ሀገራችን የኒውክለር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ መንገድ ከዓለም አቀፍ ማዕቀፎች ጋር በተጣጣመ መልኩ በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በምግብ ዋስትና፣ በጤና አገልግሎት፣ በሳይንስ እና ምርምር ዘርፎች ላይ ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት የመምራትና የማስተባበር ኀላፊነት እንዲኖረው ተደርጎ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያን ለመወሰን በወጣ ደንብ ላይ ነው፡፡ ተቋሙ የሚሰጣቸውን የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የተግባር ተኮር ሥልጠናና ማማከር እና የስፔሻላይዝድ ላባራቶሪ አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ በማቅረብ ወጪውን በሙሉ ሸፍኖ የውስጥ ገቢውን ለማሳደግ እንዲችል የአገልግሎት ክፍያ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ጽህፈት ቤትን ለማቋቋም እና የሚሰበሰበውን የፈንድ ገቢ መጠን ለመወሰን የወጣ ደንብ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ጽ/ቤት በአዋጅ ቁጥር 1386/2017 የተቋቋመውን የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ለማሥተዳደር የሚቋቋም ሲኾን የሚሰበሰበውን የፈንድ ገቢ መጠን ለመወሰን እንዲቻልም ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!