የደረሱ ሰብሎች በዝናብ እንዳይበላሹ በወቅቱ መሰብሰብ እንደሚገባ የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አሳሰበ።

7

ገንዳ ውኃ: ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በ2017/18 የምርት ዘመን ከ529 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ከ525 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

በዘር ከተሸፈነው ውስጥ ከ220 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ፣ በአኩሪ አተር፣ በሩዝ እና በማሽላ ዘር በኩታ ገጠም መሸፈኑን የተናገሩት የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ ናቸው።

ዞኑ ከፍተኛ የኾነ የቅባት እና ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎች በሰፊው የሚመረቱበት አካባቢ መኾኑንም ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ያለው የሰብል ቁመና በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና ፍሬ አያያዙ ከባለፈው ዓመት የተሻለ እንደኾነም አብራርተዋል።

በዞኑ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት እና የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኙ ሰብሎች በከፍተኛ ሁኔታ ይመረታሉ ነው ያሉት። በዋናነትም ሰሊጥ በስፋት የሚለማ መኾኑን እና አሁን ላይ ምርቱ እየተሰበሰበ እንደሚገኝም ነው ኀላፊው የተናገሩት።

ከ170 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር የተሸፈነው ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚያገለግሉ እንደ ጥጥ እና አኩሪ አተር ያሉ ሰብሎች መኾናቸውንም አስገንዝበዋል።

በደረሱ ሰብሎች ላይ የዝናብ ሥርጭቱ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር አርሶ አደሮች ከፍተኛ የኾነ የሰው ኃይል በመጠቀም ምርቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ መሰብሰብ እንዳለበት ኀላፊው ገልጸዋል።

የሚፈለገውን ምርት ለማግኘት ከብክነት ነጻ የኾነ የምርት አሰባሰብ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አቶ አንዳርጌ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሰብልን ከብክነት መታደግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው የገለጹት።

በምርት ዘመኑ ከ12 ነጥብ 6 ሚልዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አቶ አንዳርጌ ጠቁመዋል።

በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ዋላ አንገት የአገዳ እና የቅባት እርሻ ሰብሎች ማምረት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ሙሉዓለም ምልምሌ በምርት ዘመኑ 400 ሄክታር መሬት በሰሊጥ ዘር ለመሸፈን አቅደው 200 ሄክታር መሬት መሸፈናቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል።

ሌላው ቀሪውን ሄክታር በአኩሪ አተር ሰብል መሸፈናቸውንም ተናግረዋል።

ሰሊጡ ከቁመናው ጀምሮ እስከ ፍሬ አያያዙ ድረስ ጥሩ መኾኑን ባለሃብቱ ጠቁመው ከሄክታር እስከ ሦስት ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅደው እየሠሩ እንደኾነም ገልጸዋል።

አጠቃላይ በዘር ከተሸፈነው መሬት 800 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁም ነው ባለሃብቱ የገለጹት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሎተሪ ከሕግ አንጻር
Next article49ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች