
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሎተሪ እየተዝናኑ ዕድልን መሞከሪያ የሥራ እና የጨዋታ ዓይነት ነው።
ሎተሪ የሚለው ቃል የእንግሊዝኛ ቃል ነው። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት ባሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ተከታታይ ቁጥሮች የተሰጧቸው ብዙ ትኬቶች ለሰዎች ከተሸጡ በኋላ እጣ በመጣል አሸናፊ የኾነው ቁጥር የተወሰነለትን ገንዘብ ወይም እቃ በመስጠት የሚካሄዴ ተግባር ነው” የሚል ፍች ተሰጥቶታል።
ይህ ጨዋታ እንደ አንድ የንግድ ዘርፍ ተቆጥሮ በሰፊው ሢሠራ እና ተሳታፊዎችም በዕድል በሚወጣ እጣ ሃብት ለማግኘት የሚሳተፉበት ነው። ሎተሪ እና መሰል ሥራዎችን መንግሥት በሕጋዊነት የሚፈጽማቸው ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ግለሰቦችም ሲያከናውኗቸው ይታያሉ።
ግለሰቦች ያለ ሕጋዊ ፈቃድ የሚሠሯቸው የሎተሪ እና መሰል የእጣ ሥራዎች ወንጀል ናቸው ተብለውም ይፈረጃሉ። ሥራውን ያለ ፈቃድ መሥራት በራሱ ወንጀል ነው ከመባሉም በላይ ገንዘብ እየሰበሰቡ እጣ የማያወጡ እና ሌሎች ስውር ወንጀሎችን የሚሠሩም እንዳሉም ይነገራል።
በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ሙሉጌታ አሻግሬ በሎተሪ እና ዕጣ የሕግ ድንጋጌዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተውናል።
በኢትዮጵያ የሎተሪ ዕጣ ለመጀመሪያ ጊዜ በገበያ ላይ የዋለው በ1954 ዓ.ም ነው ይላሉ፡፡ የሎተሪ ሥራ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነት እና በአጨዋወት ዘዴው እያደገና እየሰፋ መጥቷል፡፡
የብሔራዊ ሎተሪ አሥተዳደር ሎተሪ የማካሄድ እና
ፈቃድ የመስጠት ብቸኛ ሥልጣን ያለው ተቋም ነው፡፡
የግሉ ዘርፍም የብሔራዊ ሎተሪ አሥተዳደር በሚሰጠው ፈቃድ በሎተሪ ሥራ መሳተፍ ይችላል ነው ያሉት።
የብሔራዊ ሎተሪ አሥተዳደርን እንደገና ለማቋቋም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ቁጥር 160/2001 አንቀጽ 2(1) መሠረት “ሎተሪ” ማለት የሽልማት አሸናፊው በዕድል፣ በእጣ አወጣጥ ወይም በማንኛውም ሌላ ዘዴ የሚታወቅበት ጨዋታ ወይም ድርጊት ሲሆን ቶምቦላን ወይም ራፍሌን፣ ሎቶን፣ ቶቶን፣ ፈጣን ሎተሪን፣ የቁጥር ሎተሪን የተደራራቢ ሽልማት ሎተሪን፣ የፕሮሞሽን ሎተሪን፣ ቢንጎን፣ የስፖርት ውርርድ ሎተሪን እና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችን እንደሚጨምር ትርጉም የተሰጠው ነው።
የብሔራዊ ሎተሪ አሥተዳደርን እንደገና ለማቋቋም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው አዋጅ ቁጥር 535/199 አንቀጽ 6(4) እና ደንብ ቁጥር 160/2001 አንቀጽ 6(5) እና 13 መሠረት እንድ አካል በሥራው ለመሠማራት የሎተሪ ሥራ ፈቃድ ማግኘት አለበት እንደሚልም ተገልጿል፡፡
በደንብ ቁጥር 160/2001 አንቀጽ 2(13) ‘በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ሀገር ማንኛውንም ሎተሪ በማዘጋጀት በሀገር ውስጥ መሸጥ፣ ማከፋፈል፣ ማጫወት እና ዕጣ ማውጣት ወይም ሌላ ተመሳሳይ ተግባራት የሎተሪ ሥራ መኾኑን ይደነግጋል። በመኾኑም እነዚህ ሥራዎች ፈቃድ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡
👉 በሎተሪ ሥራ የመሠማራት መብት እና ፈቃድ ለማውጣት የሚሟሉ ቅድመ ሁኔታዎች
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 41 /1 እና 2/ መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያውን፣ ሥራውን እና ሞያውን የመምረጥ፤ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ የመሠማራት እና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት እንዳለው ተመላክቷል፡፡
ስለኾነም ማንኛውም ሰው በተፈቀደ የሎተሪ ንግድ ሥራ የመሠማራት መብት አለው ማለት ነው፡፡
የብሔራዊ ሎተሪ አሥተዳደርን እንደገና ለማቋቋም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ቁጥር 160/2001 አንቀጽ 12 ለብሔራዊ ሎተሪ በብቸኝነት የተፈቀደ የሎተሪ ዓይነቶች እንዲሁም ማንኛውም ሰው ብቻውን እና ከብሔራዊ ሎተሪ አሥተዳደር ጋር በሽርክና የሚሳተፍባቸው የሎተሪ ዓይነቶች ተዘርዝረዋል።
የሎቶ፣ ቶቶ፣ ፈጣን ሎተሪ፣ የቁጥር ሎተሪ፣ ተደራራቢ ሽልማት እና ዘመናዊ ቢንጎን በብቸኝነት የማካሄድ ሥልጣን ያለው የብሔራዊ ሎተሪ በመኾኑ በግል አልተፈቀዱም ነው ያሉት።
ይሁን እንጅ ብሔራዊ ሎተሪ አሥተዳደር አስፈላጊ ኾኖ ሲያገኘው የሎቶ እና የቶቶ ሎተሪ ሥራዎችን ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ፣ የዕውቀት እና ሥራ አመራር ብቃት ካላቸው ተሳታፊዋች ጋር በሽርክና ሊያካሂድ ይችላል፡፡
ቶምቦላን ወይም ራፍሌን፣ የስፖርት ውድድር፣ ኮንቬንሽናል ቢንጎ እና የፕሮሞሽን ሎተሪ ሥራዎች ደግሞ በማንኛውም አካል ሊካሄዱ የሚችሉ ናቸው፡፡
በመሆኑም ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት ለብሔራዊ ሎተሪ አሥተዳደር ማመልከቻ በማቅረብ፣ አስፈላጊ የኾኑትን ቅድመ ኹኔታዎችን በማሟላት እና በመፈጸም የንግድ ፈቃድ አውጥቶ በግለሰብ ወይም በሽርክና በተፈቀደ የሎተሪ ሥራ ዓይነቶች የመሠማራት መብት አለው፡፡
👉 የወንጀል ተጠያቂነት
የብሔራዊ ሎተሪ አሥተዳደርን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ እና በወንጀል ሕጉ የሎተሪ ሥራዎችን በሕገ ወጥ መንገድ መፈጸም የሚያስከትለውን የወንጀል ተጠያቂነት አመላክቷል፡፡
የጸና የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳኖረው አንድ ሰው በሎተሪ ሥራ ላይ ተሠማርቶ የተገኘ እንደኾነ በደንቡ አንቀጽ 20 እና በአዋጁ አንቀፅ 17/1/ መሠረት በወንጀል ሕጉ ከፍ ያለ ቅጣት ከሌለ በቀር በወንጀል ተከስሶ ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከ3 እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ያስቀጣል፡፡
እንዲሁም ማንም ሰው የሕንጻ ይዞታውን ለሕገ ወጥ የሎተሪ መሸጫ እንዲውል ያከራየ ወይም በማንኛውም ሁኔታ የፈቀደ ወይም በአሥተዳደሩ ለቁጥጥር የተላከን ሠራተኛ እንዳይገባ የከለከለ ወይም የቁጥጥር ሥራው እንዳይካሄድ በማንኛውም መንገድ ያሰናከለ ከአሥር እስከ 20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እና ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ የእስር ቅጣት ይቀጣል ይላል ሕጉ።
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በሎተሪ ሥራ የተሠማሩ ሰዎች በወንጀል ሕጉ እና ሌሎች አዋጆች የተለያዩ ኀላፊነቶች አሉባቸው፡፡ የሎተሪ ፈቃድ ሳይኖረው ፈቃድ ያለው በማስመሰል መሥራት፣ የሎተሪ እጣውን አለመጣል እና ሌሎች ተመሳሳይ የማታለል ተግባራት በወንጀል ሕጉ በአታላይነት የወንጀል ኀላፊነትን ያስከትላል፡፡
አታላይነትን በተመለከተም ማንም ሰው የማይገባ ብልጽግና ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፤ አሳሳች የኾኑ ነገሮችን በመናገር የራሱን ማንነት ወይም ኹኔታ በመሰወር፤ ወይም መግለጽ የሚገባውን ነገር በመደበቅ፤ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት መጠቀም በሕግ ያስጠይቃል።
ሌላውን ሰው አታልሎ የራሱን ወይም የሦስተኛ ወገን የንብረት ጥቅም የሚጎዳ አድራጎት እንዲፈጸም ያደረገ እንደኾነ በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ከባድነት ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና መቀጮ እንደሚቀጣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 692 ስር ተደንግጓል።
ከዚህ ባሻገር የሎተሪ ሥራን እና ዕቁብን ሽፋን በማድረግ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ የንግድ ሥራዎች በንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አዋጅ 980/2008 አንቀጽ 22 እና 60 መሠረት የጸና የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳይኖር የንግድ ሥራ መሥራት ወንጀል ከአምስት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ አስራት እና ከ150 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጣ በሕጉ ተደንግጓል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!