
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፖሊዮ ወይንም የልጅነት ልምሻ በዓይን በማይታይ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው። በዓይነ ምድር በተበከለ ምግብ ወይም ውኃ ከበሽተኛ ሰው ወደ ጤነኛ ሰው ይተላለፋል።
በሽታው የነርቭ ሥርዓትን በማጥቃት የእጅ፣ የእግር ወይም የሁለቱም መዛል፣ መዘለፍለፍ፣ ዘላቂ የኾነ የአካል መስለል እንዲሁም ሞትን የሚያስከትል በሽታ ነው።
ባለፉት ሥምንት ወራት በኢትዮጵያ በ6 ክልሎች የፖሊዮ ወረርሽኝ ተከስቶ 40 የሚኾኑ ሕጻናትም በበሽታው መጠቃታቸውን የጤና ቢሮ መረጃ ያሳያል። ከእነዚህም ውስጥ ሁለቱ በአማራ ክልል የተከሰቱ ናቸዉ።
በሽታውን ለመከላከል በቅርቡም በሁለት ዙሮች በዘመቻ መልክ ክትባቱ ተሠጥቷል።
ሦስተኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ደግሞ ከመስከረም 30/2018 ጀምሮ በክልሉ በተመረጡ ዞኖች እየተሰጠ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ መሠረት በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል ተብሎም ይታሰባል። ክትባቱ እየተሰጠባቸው ከሚገኙ አካባቢውች ውስጥ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አንዱ ነው።
በከተማ አሥተዳደሩ የፖሊዮ ክትባት ካስከተቡ እናቶች ጥሩሴት በላይ አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ጥሩሴት ከዚህ በፊት ሦስት ልጆቻቸውን በዘመቻ ከሚሰጥ ክትባት ባለፈ በመደበኛም ሲያስከትቡ መቆየታቸውን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
አሁን ላይ ደግሞ ሁለት ልጆቻቸውን ቀድመው ማስከተባቸውን ነው የገለጹልን። በሽታው ለዘላቂ የአካል ጉዳት ብሎም ለሞት የሚዳርግ በመኾኑ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ “ማስከተብ ለምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ አለመኾኑን ተናግረዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ኦፊሰር አሥተባባሪ ትዕግስት ባሕሩ በሦስተኛው ዙር የፖሊዮ ዘመቻ 66 ሺህ 556 ሕጻናትን ለመከተብ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ክትባቱን በውጤት ለማጠናቀቅ ስለፖሊዮ ምንነት ቀድሞ ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
ክትባቱ ከጀመረ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2/2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ 68 በመቶ ገደማ የሚኾኑ ሕጻናትን መከተብ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይ ሁለት ቀናት የቀሩ ካሉ የማዳረስ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ክትባቱን ከቤት ለቤት ባለፈ በትምህርት ተቋማትም እየተሠጠ መኾኑን ነው የገለጹት።
በተያዘው በጀት ዓመት መደበኛ ክትባቱን 85 በመቶ ማድረስ መቻሉንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!