ፈተናዎች ያልበገሩት የቀለም ሰው

11
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በችግርም ውስጥ አልፎ በሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ከቻሉ ተማሪዎች መካከል ተማሪ አማኑኤል ዓለምነህ አንዱ ነው። ተማሪ አማኑኤል በሀገር አቀፍ ፈተናው 526 ነጥብ ማስመዝገብም የቻለ ተማሪ ነው።
ተማሪ አማኑኤል ከ9ኛ እስከ 11ኛ ክፍል በፍኖተ ሰላም ከተማ በጎጃም አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማሩንም ይናገራል፡፡
ተማሪ አማኑኤል በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ሀገራዊ ተፈታኝ ቢኾንም በነበረው ሀገራዊ ግጭት ምክንያት ሳይፈተን መቅረቱን ይገልጻል፡፡
በ2017 የትምህርት ዘመንም በአካባቢው ትምህርት ሙሉ በሙሉ ባለመጀመሩ ሁለት ዓመት ወደ ኋላ ላለመቅረት በሚል ቁጭት መሸኛ ይዞ ወደ አንከሻ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመሄድ ትምህርት መጀመሩን ተናግሯል፡፡
“ከቤተሰብ መለየት ለኔ የመጀመሪያ ጊዜየ ቢሆንም ተምሬ ጥሩ ውጤት በማምጣት ዩንቨርሲቲ መግባት ከፍተኛ ህልሜ ነበር” ይላል ተማሪ አማኑኤል።
ማንኛውንም ችግር በመቋቋም ለመወጣት ራሱን ዝግጁ አድርጎ ትምህርት ሊያገኝበት ወደሚችለው ቦታ ማቅናቱንም ያስረዳል።
ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ተማሪው ወደ ሚማርበት ቦታ አቅንቶ የሚከራይ ቤት ማግኘት ችግር ኾኖበት እንደነበርም ጠቁሟል።
የተማሪ አማኑኤልን ችግር የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪ እና የአንከሻ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር አለሙ የኔሰው በገጠመው የኪራይ ቤት ችግር ምክንያት ትምርቱ እንዳይስተጓጎል ነጻ የመኖሪያ ቤት እንደሰጡት ይናገራል፡፡
ተማሪ አማኑኤል ከነጻ ቤት መስጠት ባለፈ ይደረግለት የነበረው ቤተሰባዊ ፍቅር እና እንክብካቤ ከቤተሰብ ርቆ መኖሩ እንዳይሰማው እንዳደረገውም ገልጿል፡፡
ይህም ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ ለትምህርቱ በመስጠት እና በማጥናት ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግብ እንዳገዘው አብራርቷል።
ስለተደረገለት ድጋፍም አመሥግኗል፤ ሌሎች ተማሪዎችም ምንም አይነት ችግር ሳይበግራቸው ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም እና በርትተው በማጥናት ለውጤት እንዲበቁ መልዕክቱንም አስተላልፏል፡፡
መምህር አለሙ የኔሰው ለአሚኮ እንዳሉት ተማሪ አማኑኤል በአንከሻ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተመዘገበ በኋላ የኪራይ ቤት በማጣቱ ትምህርቱ እንዳይቋረጥ አስፈላጊውን እገዛ አድርገዋል።
ተማሪው በወቅቱ የነበረው ውጤት ከጥሩ ሥነምግባር ጋር የተሻለ ስለነበረ ለጥሩ ውጤት እንዲበቃ በማሰብ ነጻ ቤት መስጠታቸውን ነው የጠቆሙት።
በተጨማሪም መምህር አለሙ አጋዥ መጻሕፍትን እና ቤተሰባዊ ፍቅርን በመስጠት ትኩረቱ ትምህርቱ ላይ ብቻ እንዲኾን ማድረጋቸውን ነው ያብራሩት፡፡
“ባመጣው ከፍተኛ ውጤት እና ለዚህ ውጤት በመብቃት እኔ የበኩሌን አስተዋጽኦ ማድረጌም በጣም ደስ ብሎኛል” ነው ያሉ፡፡
ይህ መደጋገፍ ጥሩ መኾኑን ገልጸው አንዱ ሌላውን ቢያግዝ ሁሉም ነገር ቀላል መኾኑን የተማሪው ስኬት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም እሱ የነበረበትን ዶርም ሌሎች ተቸግረው ለሚመጡ ተማሪዎች ክፍት በማድረግ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡
የተማሪ አማኑኤል ትልቅ ወንድም አቶ መብራቱ ፈንታ ወንድማቸው ስለአማኑኤል ሲናገሩ
ሙሉ ጊዜውን ለትምህርቱ የሚሰጥ፣ ሰዓቱን በአግባቡ የሚጠቀም፣ ያልገባውን መምህራንንም ኾነ ጓደኞቹን በስልክ ሳይቀር የእያንዳንዷን ነገር ለመረዳት የሚጠይቅ ጎበዝ ተማሪ ነው ብለዋል፡፡
በሀገራዊ ችግሩ ምክንያት አንድ ዓመት በማቋረጡ ለሁለተኛ ጊዜ እንዳይደገም በራሱ ተነሳሽነት ወደ አገው ግምጃ ቤት በመሄድ መማሩን ተናግረዋል።
ከቤተሰብ ርቆ ብቻውን ሆኖ መማሩ ለችግር እንዳያጋልጠው በቤተሰቡ ስጋት ነበረ ብለዋል፡፡
ይህ ስጋት ብዙም ሳይቆይ ለተማሪ አማኑኤል ነጻ የመጠለያ ዶርም በመስጠት እንደቤተሰብ ኾነው ሊያስተምሩት የሚችሉ የአካባቢው ነዋሪ መምህር አለሙ የኔሰው ፍላጎታቸውን በመግለጻቸው ከስጋት እንዳወጣቸው ተናግረዋል፡፡
ከመምህር አለሙ የኔሰው ጋር ምንም አይነት ቤተሰባዊ ግንኙነት እንደሌላቸው እና ከዛ በፊትም እንደማይተዋወቁ የተናገሩት አቶ መብራቱ መምህሩ ቤቱን ብቻ ነጻ መስጠት ብቻ ሳይኾን ቀለብ በሚዘገይበት ጊዜ የሚያስፈልገውን በማሟላት እና የሚያስፈልገውን እንክብካቤ በማድረግ ያስተማሩት የቀለም ቤተሰቦቹ እንደኾኑም አብራርተዋል።
ይህንን መልካምነት በቃላት ብቻ መግለጽ አይቻልም፤ ትልቅ ባለውለታችን ናቸው፤ በአጠቃላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ እጅግ በጣም ጥሩ ነው ብለዋል፡፡
መምህር አለሙ ለተማሪ አማኑኤል የሚያስፈልገውን ነገር በማሟላት ያሳዩት በጎ ተግባር እንዳስተማራቸው እና እሳቸውም በትምህርት ሥራ ላይ በጎ ሥራ ለመሥራት እንዳነሳሳቸው ነው አቶ መብራቱ ፈንታ የጠቆሙት።
የአንከሻ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ደሳለው አበራ ተማሪ አማኑኤል ዓለምነህ በ2017 መጀመሪያ ከፍኖተሰላም ከተማ በሀገራዊ ግጭቱ ምክንያት ወደ አንከሻ ትምህርት ቤት ለመማር ሲመጣ ጥሩ ውጤት እንደነበረው ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱም ባለው ቦታ ተማሪውን ተቀብሎ ለማስተማር እንደፈቀደለትም ነው ያብራሩት።
ተማሪ አማኑኤል የትምህርት አቀባበሉ ጥሩ እንደነበር መምህራኑ ይገልጹ እንደነበርም ጠቁመዋል።
ትምህርት ቤቱ ተማሪ አማኑኤልን ጨምሮ 40 የሚኾኑ ጎበዝ ተማሪዎችን በመምረጥ ቅዳሜ፣ እሑድ እና የምሳ ሰዓትን ጨምሮ ቤተ መጽሐፍትን ክፍት በማድረግ ሙሉ ጊዜያቸውን እንዲያጠኑ በማድረግ፣ የተመረጡ መምህራንን በመቅጠር እና ተጨማሪ ማካካሻ ትምህርት እንዲማሩ በማድረግ እገዛ ስለመደረጉም አስረድተዋል፡፡
በዚሁ ትምህርት ቤት የሥነ ዜጋ መምህር አለሙ የኔሰው ለተማሪው አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ያደረጉት በጎ ተግባር ለሌላውም አስተማሪ ነው ብለዋል።
ተማሪውም ጥሩ ውጤት በማምጣት የትምህር ቤቱ አንደኛ በመኾን ውጤት አስመዝግቧል ነው ያሉት፡፡ በዚህም በዞንም በክልልም ከተሸለሙ ተማሪዎች አንዱ መኾን እንደቻለም ጠቁመዋል፡፡
ርዕሰ መምህሩ ተማሪ አማኑኤል በለመደው አካባቢ ሆኖ የቤተሰብ እገዛ እና ፍቅር ሳይለየው ቢማር ኖሮ ከዚህ የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ጥርጥር የለኝም ነው ያሉ፡፡
በዚህም ትምህርትን ከማንኛውም ፖለቲካ ነጻ በማድረግ ለነገ ሀገር ተረካቢ የኾኑ የተማረ ትውልድ ለማፍራት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleልጆች የፖሊዮ ክትባትን እንዲወስዱ የሁሉም ወላጆች ግዴታ ነው።
Next articleየፖሊዮ ክትባት ለምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም።