
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ፖሊዮ ወይም የልጅነት ልምሻ ክትባት እየተሰጠ ነው። ክትባቱ በ8 ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች መሰጠት ከጀመረ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ቀበሌ 16 ዋርካው ሰፈር ነዋሪ ወይዘሮ አስማሩ ታደሰ የሦስት ልጆች እናት ናቸው። ልጆቻቸውን ማስከተባቸውን ነግረውናል።
ስለ ፖሊዮ ክትባት ከአሁንም በፊት ግንዛቤ እንደነበራቸው ገልጸዋል። ክትባቱንም ሁሉም ልጆች እንዲወስዱ የሁሉም ወላጆች ግዴታ መኾኑን አንስተዋል።
ክትባቱን በመስጠት እየተሳተፉ ያሉት በጎንደር ከተማ ዞብል ክፍለ ከተማ ልደታ ቀበሌ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ሰናይት ወርቁ የፖልዮ ክትባትን ቤት ለቤት እየዞሩ እየሰጡ መኾኑን ተናግረዋል። የክትባት አሰጣጥ ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸውልናል።
አሁን ላይ ኅብረተሰቡ ስለክትባቱ ያለው ግንዛቤ ጥሩ በመኾኑ ያለምንም ቅሬታ ክትባቱ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ እንዳልክ አዳነ ለክትባቱ መሳካት ሚዲያዎች፣ መምህራን፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ርብርብ እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል። አሁንም ቢኾን ለጤናው ጉዳይ ባለቤቱ ራሱ ማኅበረሰቡ መኾኑን በመገንዘብ ወላጆች ልጆቻቸውን ማስከተብ እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቀረው ጊዜ ሁሉንም ሕጻናት በመክተብ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን