
ደባርቅ: ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ፍርድ ቤቱ የ2018 ዓ.ም የመደበኛ ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ የፍትሕ ተቋማት የሕግ የበላይነትን እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማሳደግ ሚናቸው ጉልህ መኾኑን ገልጸዋል።
የፍትሕ ተቋማቱን የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማዘመን እና ተደራሽነታቸውን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደ ዞን እየደገፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የፍትሕ ተቋማትን ተሞክሮ በማለዋወጥ እና የጋራ ሥራን በማጠናከር ለኅብረተሰባዊ ተጠቃሚነት መትጋት ይገባቸዋል ብለዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ግዛቸው ሙጬ በ2017 ዓ.ም በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በሰው ሀብት ልማት ሥራዎች የተለያዩ ተግባራት መከናዎናቸውን ገልጸዋል።
ይሄም ጥራት ያለው እና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ለማሻሻል እንደሚያስችል አብራርተዋል።
በዓመቱ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ትብብር ጥምረትን ወደ ሥራ ማስገባት እና ማጎልበት መቻሉን ገልጸዋል።
ካለው የጸጥታ ችግር አኳያ ማኅበረሰባዊ የውይይት መድረኮችን እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት ፈታኝ ኹኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።
ይኹን እንጂ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የክትትል እና ድጋፍ ሥራዎችን እና ሌሎች ተግባራት ለማከናዎን ጥረት መደረጉን አንስተዋል።
የውሳኔ ጥራትን ለማሻሻል የሚረዱ የተለያዩ ዘዴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መሞከሩን አያይዘው ገልጸዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዳኞች አሥተዳደር ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አማረ መኮንን ዳኞችን በተለያዩ አቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች የመፈጸም አቅማቸውን ለማሳደግ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የዳኝነት ሥርዓቱን ለማሻሻል ጥረት መደረጉንም አክለዋል።
በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፉ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል የኢ-ፋይሊንግ እና ስማርት ችሎት መርሐ ግብሮች በምሳሌነት እንደሚጠቀሱ ጠቁመዋል።
ከሴቶች እና ሕጻናት ጋር በተያያዘ የልዩ ችሎት አገልግሎት መርሐ ግብር በደባርቅ ወረዳ ፍርድ ቤት መተግበር መጀመሩን ገልጸዋል።
በቀጣይም የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማሻሻል የአገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት መታቀዱም ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን