
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምሥራቅ ዕዝ እና ሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሠንደቅ ዓላማ ቀንን በጋራ በባሕር ዳር ከተማ አክብረዋል።
የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉን ስናከብር የዓላማ ግልፀኝነት እና የአስተሳሰብ አንድነትን በመፍጠር ለሀገራዊ የማንሠራራት ጉዞ ስኬታማነት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ቃል በመግባት መኾን ይኖርብናል ብለዋል፡፡
በሀገራችን ሉዓላዊነትና በሠንደቅ ዓላማችን ክብር ላይ የማንደራደር፣ የምንፈፅመው ግዳጅ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ነፃነት እና የግዛት አንድነት ከማስጠበቅ ተልዕኳችን ጋር የተቃኘ መኾን አለበት ነው ያሉት።
የተጀመሩ ግዳጆችንን በላቀ ብቃት መፈፀም የሚያስችሉ አካላዊ፣ ቴክኒካዊ እና ሥነ ልቦናዊ ዝግጁነት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የምሥራቅ ዕዝ እና የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሠራዊት አባላት “ሠንደቅ ዓላማችን የሀገራችን እና የማንነታችን መለያ ነው” ብለዋል። ሠንደቅ ዓላማ የነፃነታችን ምልክት እንደመኾኑ መጠን እና ለሠንደቅ ዓላማችን መደረግ ስለሚገባው የክብር ሥነ ሥርዓት ጠንቅቀን የተረዳን በመኾናችን ከቅደመ አያቶቻችን የወረስነውን ጀግንነት ማስቀጠል አለብን ብለዋል፡፡
በባሕር ዳር የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ሠንደቅ ዓላማ መስቀል እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙርም የመዘመር መርሐ ግብርም ተከናውኗል።
መረጃው የምሥራቅ ዕዝ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን