
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቢሾፍቱ ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባለፉት ሁለት ዓመታት የሰላም ችግር ቢያጋጥምም ሰላሙን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ቢሮዎችን ለሥራ ምቹ ከማድረግ ጀምሮ የጣናን ዳር የማልማት፣ የኮሪደር ልማት፣ የቄራ ፕሮጀክት ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን ገልጸዋል።
የተሠሩ የልማት ሥራዎች የጎብኝዎችን ቆይታ የሚያራዝሙ መኾናቸውን ተናግረዋል። ጉብኝቱ የሁለቱን ከተሞች ሕዝብ የሚያስተሳስር እንደኾነም ገልጸዋል።
በቀጣይም የሕዝብ ለሕዝብ ጉብኝት ለማካሄድ ይሠራል ነው ያሉት።
የቢሾፍቱ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ዓለምአየሁ አሰፋ በጣና ሐይቅ ዙሪያ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የባሕር ዳርን የተፈጥሮ ውበት ይበልጥ የሚያደምቁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ከተማዋን በተደጋጋሚ እንደጎበኙ የገለጹት ከንቲባው አሁን ላይ የተሠሩ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እንደሚያሳድጉ ተናግረዋል።
የልማት ሥራዎቹ የወደፊቱን የከተማዋን ዕድገት ታሳቢ ያደረጉ እና ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ እንደሚኾኑም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!