
ጎንደር፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ”ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ መልዕክት በልዩ ልዩ ወታደራዊ ትዕይንት አከብሯል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ የሉዓላዊነት ተምሳሌት የኾነውን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ ለማድረግ መስዋዕትነት የከፈሉ በርካታ ጀግኖች መኖራቸውን ተናግረዋል።
የቀደሙ ጀግኖች የውጭ ጠላቶችን ድል ነስተው ነጻነቷ የተረጋገጠ ሀገር ለትውልድ አስረክበዋል ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ለሠራዊቱ ትልቅ ትርጉም አለው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ “በሠንደቅ ዓላማ ፊት የገባነውን ቃል ጠብቀን ሀገራችንን በመጠበቅ ለቀጣይ ትውልድ እናስረክባለን፤ ሠንደቅ ዓላማውም ልዩ ትርጉም አለው” ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ከውጭም ከውስጥም ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም የሠንደቅ ዓላማዋ ክብር ተጠብቆ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገር ትቀጥላለች ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አባላት የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማን ሲመለከቱ ሕዝብ፣ ሀገር፣ ነጻነት እና ኢትዮጵያዊነትን አንድ ላይ እንደሚያስቧቸው ጠቁመዋል። ሀገራቸውን በጽናት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
በጀግንነት ነጻነቷ ተረጋግጦ የተረከቧትን ሠንደቅ ዓላማ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያላቸውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።
“ሀገር በመስዋዕትነት፣ በጀግንነት እና በድል ከፍ ትል ዘንድ በሠንደቅ ዓላማዋ ፊት ቃል ገብተናል” ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ቃልኪዳን ኀይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!