
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ መልዕክት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ነው፡፡
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሠራተኞች እና መሪዎችም የሠንደቅ ዓላማ ቀንን አክብረዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አማካሪ ግዛቸው ሙሉነህ “ሠንደቅ ዓላማችን የአንድነታችን አርማ፣ የአብሮነታችን ቃል ኪዳን፣ የሀገራችን መገለጫ ምልክት ነው” ብለዋል።
በየዘመናቸው ኢትዮጵያውያን ታግለው፣ መስዕዋትነት ከፍለው፣ በደማቸው እና በአጥንታቸው ያቆሟት እና ታሪክ የሠሩባት የኢትዮጵያ መገለጫ መኾኗን ገልጸዋል።
አያት ቅድመ አያቶች ዋጋ እየከፈሉ በትውልድ ቅብብሎሽ ለአኹኑ ትውልድ እንዳስረከቧትም አብራርተዋል።
የአሁኑ ትውልድ በየተሠማራበት ሁሉ ሰላምን በማስጠብቅ፣ ልማትን በማስቀጠል እና በታማኝነት አገልግሎት በመስጠት ለሠንደቅ ዓላማ ያለውን ክብር መግለጥ እንደሚገባውም ገልጸዋል።
የቀደመ ታሪክን በመረዳት የራስን ታሪክ በመሥራት ለሠንደቅ ዓላማ ታማኝ ኾኖ አገልግሎት መሥጠት እንደሚገባም አንስተዋል።
የሠንደቅ ዓላማ ቀን በተቋሙ ሲከበር ለማኀበረሰቡ ተገቢውን መረጃ ከማድረስ ጀምሮ ወደ ለውጥ ጎዳና እንዲጓዝ የሚያስችል ሥራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሥልጠና እና ምርምር ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ጥላሁን ቸሬ ሠንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር ምልክት ነው ብለዋል።
በሠንደቅ ዓላማ ውስጥ ብዙ መልዕክት አለ ያሉት ጋዜጠኛ ጥላሁን ሕዝብ፣ ባሕል፣ እሴት እና ታሪክ ሁሉ የሚወከሉት በሠንደቅ ዓላማ መኾኑን አንስተዋል።
ሠንደቅ ዓላማን ማክበር ማለት ሀገርን መውደድ ነው፤ የሀገር መውደድ መገለጫው ሁሉም በየተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ተግቶ መሥራት ነው ብለዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ፍሬ ሕይወት ይልቃል የሠንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር የሀገር ፍቅር የሚገለጸው በተመደቡበት የሥራ ዘርፍ በፍትሐዊነት መሥራት፣ ግዴታን መወጣት እና ውጤታማ ኾኖ በመገኘት ነው ብለዋል።
ሀገር ወዳድ ትውልድ ለመገንባት ልጆች ሀገራቸውን እንዲወዱ በመቅረጽ እና ኮትኩቶ በማሳደግ ሴቶች ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ዜጎች ለሠንደቅ ዓላማ የበለጠ ክብር እንዲኖራቸው እና የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲሰርጽ ለማድረግ በትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ልጆች ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!