
ገንዳ ውኃ፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ መልዕክት ተከብሯል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር አፈ ጉባኤ ጋሻ አራገው የሠንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር ለሀገር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን ማስታወስ እና መዘከር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሠንደቅ ዓላማ የብሔራዊ አንድነት እና የሉዓላዊነት መገለጫ አርማ ምልክት ነው ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማ ብሔር፣ ሃይማኖት እና ቀለም ሳይባል ሁሉም ሊያከብረው እና ክብር ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት። ሠንደቅ ዓላማው በሚወጣበት እና በሚወርድበት ጊዜ ማክበር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ሕዳሴ ግድብን በኅብረት እና በጽናት እንዳሳካን ሁሉ ሌሎች ተስፋ ሰጭ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የተጀመሩ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የሦሥቱ ቀበሌ አስተባባሪ ሳጅን ጋሻው ፈለቀ በሠንደቅ ዓላማው ክብር ጀግኖች አባቶች እና አርበኞች ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ለሀገር ነጻነት የከፈሉትን መስዋዕትነት ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል። ቀኑን በተለየ ሁኔታ ማክበር እንደሚገባም አንስተዋል።
ሠንደቅ ዓላማ የነጻነት አርማ፣ የሉዓላዊነት ማንጸባረቂያ እና የሀገር ክብር ኩራት መኾኑንም ሳጅን ጋሻው ተናግረዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙልየ አየልኝ ሠንደቅ ዓላማ የአንድነት ድምቀት እና የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው ብለዋል።
ትውልዱ ስለ ሠንደቅ ዓላማ ክብር ማወቅ እና ማክበር እንዳለበት ገልጸዋል። ልጆች ሀገር ወዳድ እንዲኾኑ እና ለሀገር ክብር እንዲቆሙ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!