
ሰቆጣ፡ ጥቅምት 03/2018ዓ.ም (አሚኮ) 18ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን በሰቆጣ ከተማ “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፤ ለብሔራዊ አንድነታችን፤ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ነው።
የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ሲያከብሩ አሚኮ ያገኛቸው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አበባው መኮነን ሠንደቅ ዓላማችን አባቶቻችን በደማቸው ያቆዩት የአንድነታችን ማጽኛ የጋራ መለያችን ነው ብለዋል።
ሠንደቅ ዓላማን ማክበር ከአሁኑ ትውልድ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ሲያከብሩ አሚኮ ያገኛቸው ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ኮማንደር አበጀ አሰፋ “ሀገር የሚወከለው በሠንደቅ ዓላማ ነው” ብለዋል። የሀገር መገለጫን መጠበቅ እና ማስጠበቅ የወጣቱ ትውልድ ኀላፊነት መኾኑንም አስረድተዋል።
ቀደም ሲል በየመስሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ይሰቀል ነበር፤ ሠንደቅ ዓላማው ሲሰቀልም ሁሉም በየአለበት በመቆም ያለውን ክብር ይገልጽ ነበር ነው ያሉት።
ኮማንደር አበጀ አሰፋ ዛሬም ይህንን ልምድ መመለስ እና ለሠንደቅ ዓላማ ክብር መስጠት እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።
በሠንደቅ ዓላማ አከባበር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ “የሠንደቅ ዓላማ ቀን ዜጎች የጋራ እሴቶቻቸውን የሚያጠናክሩበት እና አንድነታቸውን የሚያሳዩበት ልዩ ሀገራዊ በዓል ነው” ብለዋል።
በሠንደቅ ዓላማ ፊት በመቆም ለሀገር ዕድገት እና ሰላም መጽናት በጋራ ለመሥራት እና ለሠንደቅ ዓላማ ያለን ፍቅር ለማረጋገጥ ቃለ መሐላ የሚገባበት ቀን እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ ፦ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!