ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አንቺን የናቁት ወድቀዋል፤ አንቺን ያከበሩት ከብረዋል፤ አንቺን የነኩት ተቃጥለዋል፤ አንቺን የገፉት ተዋርደዋል፤ አንቺን የወጉት ተወግተዋል። በአንቺ ላይ የዘመቱት አልቀዋል፤ በዓለሙ ፊት እንደ ትቢያ ተበትነዋል።
ለአንቺ የቆሙት ጸንተዋል፤ ለአንቺ የዘመቱት ድል አድርገዋል፤ ለአንቺ የወደቁት በወርቅ ቀለም ተጽፈዋል፤ በማያረጅ አለት ላይ ተቀርጸዋል፤ በማይጠፋ መዝገብ ላይ ሰፍረዋል።
አንቺን ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ጀግኖች ቆስለው አክመውሻል፤ ወድቀው አቁመውሻል፤ ሞተው አኑረውሻል፤ ጸንተው አጽንተውሻል፤ ታምነው አኑረውሻል፤ ስለ ክብርሽ መከራውን ችለዋል፤ ስለ ፍቅርሽ ሞትን ንቀዋል፤ ስለ ረቀቀ ሚስጢርሽ ደስታን ትተዋል፤ ድሎትንም ረስተዋል።
አንቺን ያዩ ነጻነትን ያያሉ፤ አንቺን የተመለከቱ ድልን ይመለከታሉ፤ አንቺን ያዩ አሸናፊነትን ያያሉ፤ አንቺን ያስታዋሉ ጥንታዊነትን ያስታውላሉ፤ አንቺን የተመለከቱ ክብር እና ልዕልናን ይመለከታሉ፤ አንቺን ያዩ የሥልጣኔን መንገድ ያያሉ።
አንቺን የተከተሉ ታላቅነትን ይከተላሉ፤ በአንቺ ጎዳና የተጓዙ ድልን ይጨብጣሉ፤ ነጻነታቸውንም ያጸናሉ፤ ሉዓላዊነታቸውን ያስጠብቃሉ፤ ሀገራቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ባሕላቸውን፣ እሴትና ሃይማኖታቸውን ከነጣቂ ተኩላ ይጠብቃሉ።
አንቺ የጥቁሮች ምልክታቸው፤ የነጻነት አብነታቸው፤ የሉዓላዊነት አርዓያቸው ነሽ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩዋ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ።
አንቺ በቀደምሽበት ሁሉ የነጻነት ጮራ ይበራል፤ አንቺ ባለሽበት ሁሉ ድል ይበሠራል፤ አንቺ በታየሽበት ሁሉ አሸናፊነት ይነገራል፤ አንቺ ከፍ ብለሽ በታየሽበት ጊዜ ሁሉ ጠላት ይሸበራል፤ አንቺ በተገለጥሽበት ሁሉ ቃል ኪዳን ይጸናል፤ ኢትዮጵያዊነት ይጠነክራል። አንቺ በታየሽበት ሁሉ ጥቁር ሁሉ ምልክቴ እያለ ይኮራል።
የኢትዮጵያ ተራራዎች አንቺን ካላውለበለቡ አይደምቁም። ኢትዮጵያውያን አንቺን ካላዩ ከአንጀታቸው አይስቁም። ያለ አንቺ ደስታቸውን አያደምቁም።
አንቺ በከፍታው አናት ላይ እንዳትወርጅ ኾነሽ ተሰቅለሻል፤ በኢትዮጵያውያን ልብ ላይ ታተመሻል፤ እንዳትጠፊ ኾነሽ ተቀርጸሻል። አበው በታላቅ ክብር ለልጅ ልጅ ያወርሱሻል፤ ልጆችም ውርሳቸውን ተቀብለው አብዝተው ይጠብቁሻል።
ኢትዮጵያውያን ሠንደቅ ዓላማቸውን አብዝተው ይወዷታል። ሲኖሩ ይደምቁባታል፤ ከፍ ከፍም ይሉባታል፤ በኩራት ያውለበልቧታል፤ በፍቅር ይጠብቋታል፤ እናቶች በቀሚሳቸው እና በነጠላቸው ጫፍ ላይ እያቀለሙ ያጌጡባታል፤ አባቶች በጋቢያቸው ጫፍ ላይ እያሠሩ ይዋቡባታል።
በሞቱም ጊዜ ከፈናቸው አድርገው ይቀበሩባታል። ለሠንደቅ ዓላማቸው ያላቸው ፍቅር ሲኖሩ ብቻ አይደለም ሲሞቱም ሁሉ ነው እንጂ።
ኢትዮጵያውያን ሠንደቃቸውን በሰማይ ተስላ ያዩዋታል፤ በምድርም በተራራው አናት ላይ ይመለከቷታል። ለዚያም ይመስላል።
“ሠንደቅ ዓላማችን ቀስተ ደመና ነው
በሰማይ ተሰቅሏል ዓለም ሁሉ እንዲያየው” እያሉ የሚቀኙት። ሠንደቅ ዓላማችን ቀስተ ደመና ናት፤ ምድር እና ሰማይ የተገናኘባት፤ ሰውና ፈጣሪ በቃል ኪዳን የተሳሰረባት እያሉ ይናገራሉ።
“ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፤ ቀስቴን በደመና አድርጌያለሁ፤ ይህም የቃል ኪዳን ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይኾናል። በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች” ተብሎ እንደተጻፈ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ ከሰማይ የተሰጠች፤ በሰማይ ላይ የተዘረጋች የቃል ኪዳን ምልክት ናት ይላሉ ኢትዮጵያውያን።
ንቡረ ዕድ ኤርሚያስ ከበደ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያውያን ሕልውናቸው ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ የቀስተ ደመናውን ምልክት በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ ፈጣሪያቸው በመካከላቸው ለመገኘቱ መተማመኛቸው ነው።
ኢትዮጵያውያን በአፋዊው ዓይነ ሥጋቸውና በውስጣዊ ዓይነ ሕሊናቸው ዘወትር ወደዚህ ወደ ቀስተ ደመናው ምልክት አተኩረው የሚመለከቱት ያለ በቂ ምክንያት አይደለም።
ይልቅ በሠንደቅ ዓላማው ከፈጣሪያቸው ጋር የቃል ኪዳን ስምምነት ያላቸው መኾኑን፤ ያም ቃል ኪዳን መከለያ ኾኖ ከጠላት የሚጠብቃቸው መኾኑን፤ ከእልቂት የሚተርፉበት ረቂቅ መጠለያቸው ያ ቃል ኪዳን መኾኑን ስለሚያምኑበት ነው ይላሉ።
በቀስተ ደመና አምሳል የረቀቀችው የቃል ኪዳኗ ሠንደቅ የደኅንነት መተማመኛችን፤ ዋስትናችን፣ ምስክራችን ናት ይሏታል።
ንቡረ ዕድ ኤርሚያስ ሲጽፉ ኢትዮጵያውያን ሀገር፣ ሕዝብ እና መንግሥት ኾነው መኖር ከጀመሩበት ዘመን ጀምሮ ከኖህ በውርስ የተቀበሉትን ቀስተ ደመና ፈጣሪያቸው እንደ ቃል ኪዳኑ በየልባቸው ጽላት ላይ ጽፎት እና በልባቸው ውስጥ አሳድሮባቸው እርሱን አምላካቸውን በእውነት እና በመንፈስ ሲያስቡበት ኖረዋል።
እንዲህ እየኖሩ ሳሉ በኋላ ዘመን ለሕዝብ ማንነት መታወቂያ እና ለሀገር ምንነት መለያ የሚኾን ብሔራዊ እና መንግሥታዊ ምልክት አዘጋጅቶ ማውጣት አስፈላጊ የኾነበት ጊዜ ሲደርስ ይህንኑ የቀስተ ደመና ኪዳናዊ ምልክት የሚተካ ሌላ ሰው ሠራሽ ሠንደቅ ዓላማ መፈልሰፍ አላስፈለጋቸውም።
ከዚህ ይልቅ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የቀስተ ደመናው መደበኛ እና አጠቃላይ፣ ዓበይት እና ደማቅ የኾኑትን አረንጓዴን፣ ቢጫ እና ቀይ ኅብረ ቀለማት የያዘ ኾኖ እንዲዘጋጅ በመወሰን የቃል ኪዳኑ ምልክት በሠንደቅ ዓላማነት ጸንቶ እንዲቀጥል አደረጉ ብለው ጽፈዋል።
የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ አርማቸው እና ሕዝባዊ ምልክታቸው አድርገውት እንደኖሩት ሁሉ ተከታዩም ትውልድ የአባቶቹን ቃል አጽንቶ እስከዛሬ አዝልቆታል።
ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የመለያ ሠንደቅ ዓላማ የነበራት ሀገር ናት ብለው ጽፈዋል።
የቀደሙ አባቶች እና እናቶች ዓድዋን የመሰለ ድል የተቀዳጁት፣ ከዓድዋም አስቀድሞ በነበሩት ተጋድሎዎች ሁሉ ሁሉንም በድል የተወጡት፣ ከዓድዋ በኋላም ሀገሬን አላስደፍርም ብለው ነጻነታቸውን ያስከበሩት፤ ሉዓማዊነታቸውን ያስጠበቁት አረንጓዴ ፣ ቢጫ፣ ቀዩዋን ሠንደቅ ዓላማ እያስቀደሙ ነው።
እነኾ ከእነርሱ ቃል ኪዳን እና የሀገርን አደራ የተቀበለው የዛሬው ሠራዊትም ሠንደቅ ዓላማዋን አስቀድሞ በምሽግ ውሎ በምሽግ ያድራል። ስለ እርሷ ክብር እና ፍቅር በጽናት ቆሟል።
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ ዓላማ ወጀብ የማያናውጻት ቤት ናት ኢትዮጵያውያን የሚሠባሠቡባት፤ ሰላምን የምትሰጥ ጥላ ናት ኢትዮጵያውያን የሚያርፉባት፤ ከሁሉ የተለየች ምልክት ናት ኢትዮጵያውያን የሚታወቁባት፤ የማታረጅ ጌጥ ናት ኢትዮጵያውያን የሚደምቁባት፤ አብዝተው የሚያጌጡባት፤ የማትበጠስ ምስጢራዊት ገመድ ናት ኢትዮጵያውያን ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ የተሳሰሩባት፤ የአንድነታቸውን ውል ያጠበቁባት፤ የረቀቀች ተራራ ናት ኢትዮጵያውያን ከፍታቸውን የሚገልጹባት፤ ፊደል ናት ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን፣ ድል አድራጊነትን እና አይበገሬነትን የተማሩባት፤ ዓለት ናት መሠረታቸውን ያጸኑባት።
ኢትዮጵያውያን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሠንደቃቸውን ዘወትር ያስቧታል። ዘወትርም ይጠብቋታል። ዘውርትም ይመኩባታል። በሰርክ ለእርሷ ይቆሙላታል። ለክብሯ መገለጫ ሲሉ ደግሞ በዓመት አንድ ቀን የሠንደቅ ዓላማ ቀን ብለው ያከብሯታል። እነኾ ያቺ ቀን ዛሬ ናት። ኢትዮጵያውያን በክብር ቆመው ለሠንደቅ ዓላማቸው ክብር እየሰጡ ነው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሠንደቅ ዓላማ ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፈው መልዕክት ሠንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር መንግሥት እና ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ሥልጣን፣ ነፃነት፣ ዕድገት እና ማኅበረሰባዊ ትስስር መፍጠሪያ መሣሪያ ነው ብሏል።
ሠንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ የታተመ የሀገራዊ አንድነት እና ነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ ነው፡፡ የአንድነታችን እና የኅብረታችን ማሳያ፣ ጀግኖች አያቶቻችን ወራሪዎችን አሸንፈው ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የኾነውን ሠንደቅ ዓላማ የሕይዎት መስዋዕትን ከፍለው ለአዲሱ ትውልድ አስረክበዋል ነው ያለው። ይህም ትውልድ በጽናት ይጠብቃታል፤ በኩራት ያከብራታል።
ለክብርሽ እጅ ይነሳልሻል፤ ለፍቅርሽ ክቡር መስዋዕትነት ይከፈልልሻል። ስለ ምን ቢሉ አንቺ የነጻነት አርማ፣ የቃል ኪዳን ምልክት ነሽና።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!