
ደሴ: ጥቅምት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 14ኛው ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የሰላም አገልግሎት ሥልጠና በወሎ ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ነው።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዲን ብርሃኑ ግርማ (ዶ.ር) የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጊዜን፣ ጉልበትን እና ዕውቀትን ሳይከፈልበት ለሌሎች ማካፈል ማለት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የሠለጠነ ዜጋ በሀገሩ ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና ውስጥ ባለቤት ኾኖ የሚሳተፍበት ወርቃማ መንገድ ነው ብለዋል።
ከሥልጠናው የሚገኘው ዕውቀት እያንዳንዱ በጎ ፈቃደኛ ለሌሎች ብርሃን እንዲኾን እና ተስፋን እንዲዘራ ዕድል ይሰጣል ነው ያሉት።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሥልጠናው ውጤታማ እንዲኾን አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብ እና አሠልጣኞችን በመመደብ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እየሠራ መኾኑን በዩኒቨርሲቲው የአሥተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት አማካሪና የምክትል ፕሬዝዳንቱ ተወካይ ጌትነት ካሴ ተናግረዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አማካሪ አበበ ወርቁ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። መርሐ ግብሩ ወጣቶች በምክንያታዊነት እንዲያምኑ በማድረግ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እና ሀገራዊ አንድነት ለማምጣት ቁልፍ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በሁሉም ክልሎች ካሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት በማድረግ ሰላምን ለማጽናት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሠልጣኞች ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማጽናት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ለቀጣይ ተልዕኳቸው ውጤታማነት ይረዳቸው ዘንድ ሥልጠናውን በአግባቡ እንዲከታተሉም አሳስበዋል። እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶች ሥልጠና ወስደው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመሰማራት ሀገራዊ መግባባት እና አንድነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሰላም፣ የፍቅር እና የብልጽግና ምሳሌ ኾና እንድትቀጥል ወጣቶች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
ከሥልጠናው በሚያገኙት ግብዓት ታግዘው በሚሰማሩበት አካባቢ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን እንደሚሠሩ የሥልጠናው ተሳታፊ ወጣቶች ገልጸዋል።
ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና አንድነትን ለማጠናከር እንደሚሠሩም ወጣቶቹ አንስተዋል። ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሰባሰቡ በመኾኑ አንዱ የሌላውን ቋንቋ እና ባሕል አውቆ ውጤታማ የሰላም እሴት ግንባታ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ለብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሠልጣኞች የሚሰጠው ሥልጠና ለአንድ ወር እንደሚቆይም ተመላክቷል።
ዘጋቢ:-አሊ ይመር
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን