
ደብረ ብረሃን: ጥቅምት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የግሪሳ ወፍ መከሰቱን አስታውቋል።
የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እጅጉ ምንከፌ ከሳምንት በፊት በምልከታ ደረጃ የታየው የግሪሳ ወፍ ከሦስት ቀን ወዲህ መጠኑ መጨመሩን ተናገረዋል።
አሁን ላይ የማሽላ ሰብል ፍሬ የሚያወጣበት በመኾኑ ከወዲሁ እርጭት ካልተደረገ ጉዳቱ ከፍተኛ እንደሚኾን ነው ኀላፊው የገለጹት።
በአጎራባች ወረዳዎች ማለትም ጅሌ ጥሙጋ እና ቀወት ወረዳም በተመሳሳይ ችግሩ መከሰቱን ተናግረዋል።
በወረዳው ነጌሶ እና ጀውኃ በተሰኙ ሁለት ቀበሌዎች 420 ሄክታር መሬት ያካለለ ስፍራ ላይ ችግሩ ማጋጠሙን ተጠቁመዋል፡፡
በወረዳው ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በማሽላ የለማ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው በአሁኑ ሰዓት ሰብሉ በአበባ ደረጃ ላይ እንደኾነና የግሪ ወፍ ክስተቱን መቆጣጠር ካልተቻለ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ኀላፊው አጽንኦት ሰጥተዋል።
አስቀድሞ ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን የሚያጠቃው የጢንዝዛ ሰብል ተከስቶ ከ90 በመቶ በላይ የሚኾነውን በባሕላዊ መንገድ እና በኬሚካል ርጭት ማስወገድ መቻሉን አስተውሰዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው ቁጥሩ እስከ 3 ሚሊዮን የሚገመት የግሪሳ ወፍ በኤፍራታ እና ግድም እንዲሁም ቀወት ወረዳዎች መታየቱን ገልጸዋል።
በጊዜያዊነት በባሕላዊ መንገድ ግሪሳ ወፉ ማሽላ ሰብል ላይ እንዳያድር የማድረግ ሥራ ይጠይቃል ነው ያሉት።
በአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ ሸዋ ሮቢት ያለውን የአውሮፕላን ማረፊያ የማጽዳት እና የጥገና ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር ሌላኛው አማራጭ ከኮምቦልቻ አየር ማረፊያ መጠቀም የሚቻልበትን ዕድል ከክልል ግብርና ቢሮ ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል ቡድን መሪው።
ዘጋቢ:- በላይ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!