
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመን ዘመንን እየወለደ በሄደ ቁጥር የሰው ልጅ የፈጠራ ጥበብ እና የቴክኖሎጅ አጠቃቀምም አብሮ እየረቀቀ መሄዱ አይቀሬ ነው። ለሰው ልጆቾ ግልጋሎት እየሰጡ ካሉ የቴክኖሎጅ ትሩፋቶች ውስጥ የሞባይል ስልክ አንዱ ነው።
በእኛ ሀገር በተጀመረበት ወቅት አገልግሎት ላይ የዋለው የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች የመንግሥት ባለሥልጣናት እና በንግዱ ዘርፍ የተሠማሩ ጥቂት ባለሃብቶች ነበሩ ለማለት ያስደፍር ነበር። አሁን ደግሞ ብዙኃኑ ተጠቃሚ ኾኗል። ጉዳዩ ታድያ ሕጻናትንም ጨምሯል።
በወቅቱ የሞባይል ስልክ አገልግሎቱ ንግግር ብቻ ነበር ፡፡አሁን ደግሞ የሞባይል ቴክኖሎጂው ከድምጽ፣ ከጽሑፍ መልዕክትም በላይ ኾኗል። ገቢ ማግኛ፣ መገበያያ፣ ወዳጅ መፍጠሪያ፣ መረጃ ማግኛ፣ የመረጃ ማጠራቀሚያ፣ ጓደኛ፣ መማሪያ፣ ሕጻናት ሲያለቅሱ ማባበያ እንዲሁም እንቅልፍ ማስተኛም ሲኾን ይስተዋላል።
ከአዋቂዎች እስከ ሕጻናት ድረስ ከሕይወታችን ጋር ተቆራኝቷል ማለት ይቻላል፡፡ አስተዋጽኦው ጉልህ ቢኾንም እንኳ አጠቃቀማችን ግን ብዙ ክፍተቶች የሚታይበት ነው። ከአጠቃቀም ክፍተቶች መካከል ደግሞ የሕጻናት የሞባይል ስልክ አጠቃቀም የትዝብቴ መነሻ ሃሳብ ነው።
ቤተሰቦቼ ውስጥ ካሉ ልጆች አንደኛው ዕድሜው ሦስት ዓመት ነው። ብዙ አያለቅስም እንጅ ካለቀሰ የሚታለለው በስልክ ብቻ ነው። ምግብ አልበላም ብሎ ሲያስቸግርም ስልክ እንድትሰጥህ ተብሎ ነው የሚመገበው። አብሶ ቲክቶክ ለእሱ አፒታይዘር (የምግብ ፍላጎት መጨመሪያ ቪታሚን) ነው ብል ማጋነን አይደለም።
ስልክ ከሌለ ምግብ ብላ አትብላ ግልግሉ አይድረስ ነው። እኔ አልሰጥም ስልኬን ስል ሌላኛው የቤሰብ አባል የለቅሶ ድምጽ ላለመስማት ይሰጣል። አንዱ ስህተት እዚህ ላይ ነው። እሱ ብቻ እንዳይመስላችሁ አሁን ላይ ብዙ ሕጻናት ይህንኑ ሁኔታ ይጋሩታል። ስልክ የሌለ ቀን ግን ምን ሊኾኑ ነው? ወላጆች ጉዳዩን እያሰብንበት እላለሁ።
የአንድ ጎረቤቴ ልጅ ደግሞ ዕድሜው ለሁለት ዓመት የተጠጋ ነው። በተደጋጋሚ ስመለከተው ረጅም ሰዓት ከስልክ ጋር ተቋራኝቶ ነው። ከዕለታት አንድ ቀን ወላጅ እናቱን ምነው ለዚህ ትንሽየ ልጅ የሞባይል ስልክ ሁሌ የሚል ጥያቄ አነሳሁላት። የዘመኑ ልጆች የስክሪን ትውልድ ናቸው፤ ምንም ማድረግ አይቻልም የሚል ምላሽ ሰጠችኝ።
ግን እኮ ማድረግ የምንችለው ነገር አለ። የአንድ ቤተሰብ አባል የጋራ በሚያደርገን ሳሎን ላይ ሁነን በየፊናቸን ስልካችን ላይ አፍጥጠን ጆሯችን ቢቆርጡን የማንሰማ እናት እና አባት፤ እህት እና ወንድምን የተመለከተ ልጅ ምን እንዲኾን ፈልገን ነበር? ንጹሕ ወረቀት ላይ እያስቀመጥነው ያለውን አሻራ እናስብ የሚለው የኔ ትዝብት ነው።
በቅርቡ ደግሞ ወደ አንድ ቅርብ ዘመድ ቤት ጎራ ብየ ነበር። የአምስት ዓመት ዕድሜ አካባቢ ያለች ሕጻን ቤት ውስጥ ነበረች። ለሰላምታ እጀን ስዘረጋ ሳትመልስልኝ ስሜን ጠርታ ስልክሽ ጌም የለውም? አለችኝ። እኔም አወ የለውም አልኳት። ቲክቶክስ አለችኝ የለውም አልኳት። ለምን? እንዴት? እያለች ጥያቄዎቿን አከታትላ ጠየቀችኝ።
ግን እኮ ስልኬ ላይ ቲክቶክ አለ። እንደ አስፈላጊነቱ እጠቀማለሁ። አልጠቀምም ያልኳት በምክንያት ነው። ምንም ይሁን ምን ለመከልከሌ ልጅ ናትና በጎ ምክንያት ልሰጣት ፈለግሁ። ምክንያቴን መንገር ስጀምር ግን ቤት ውስጥ ድግስ ነበር እና አንድ ተጋባዥ እንግዳ ሰላምታ ሰጦ ሲገባ ንግግሬን ሳታስጨርሰኝ እየሮጠች ሄዳ ተጠመጠመችበት።
ለካ ወደ ቤታቸው ሲመጣ ስልክ የሚሰጥ የእርሷ መልካሙ ሰው ነው። ከእርሱ ውጭ ዘመድ ያላት አልመሰለችም። እኔ የተጠየቅሁት ጥያቄ ወደ እርሱ ዞረ። እርሱም ልምዷን ያውቃልና ስልኩን ሰጣት።
ሁላችንም እንግዳ ሲመጣ ሰውየውን ሳይኾን ስልኩን የሚናፍቁ ልጆች እየፈጠርን ነውና እናስብበት!።
ትዝብቴን ልቀጥል ሕጻኗ ከቤታቸው እንግዳ የተቀበለችውን ስልክ ይዛ በፍጥነት መቀመጫ ወንበር ፈለገች። እኔ ቀድሜ ወንበር ላይ ተቀምጨ ነበር። ከጎኔ ነበር የተቀመጠች። ስልኩን ከፍታ የቲክቶክ ገጹን መጎብኘት ጀመረች።
አንዳንዴ አስቂኝ፣ አንዳንዴ አስፈሪ፣ አንዳንዴ አስተማሪ ተንቀሳቃሽ ምስል (video) ማየት ጀመረች። የምታሳልፍበት ፍጥነት ለጉድ ነው። አንዳንዴ ቆም ብላ አንዳንዴም ደግሞ ወደ ኋላ መልስ ብላ ታይ ነበር። የሚገርመው አስፈሪ እንስሳ እያየች እንኳ ምንም አልመሰላትም። እኔ ግን ሰቅጥጦኛል። ለልጆች የሞባይል ስልክ ስንሰጥ የሚያዩትን እና የሚሞክሩትን ነገር መምረጥ አለብን እላለሁ!።
በግሌ ፍጹም ከስልክ መራቅ አለባቸው የሚል እምነትም የለኝም። አጠቃቀማቸው ላይ እንጠንቀቅ እንጅ! ምክንያቱም ለአንዳንድ ልጆች ስልክ የዕውቀት በር ኾኖ ያገለግላቸዋል። ዓለምን ያስቃኛቸዋል። ከወላጅ እና ከመምህራን ያላገኙትን መረጃ ያጋራቸዋል። አዕምሯቸው ብዙ እንዲገረም ብዙ እንዲያስስ ያደርጋቸዋልና።
የስልክ ስክሪን ላይ የሚያፈጡበትን ጊዜም መወሰን አለብን። እንደታዘብኩት የልጆቻችን የስክሪን ቆይታ በበዛ ቁጥር ካላቸው እንቅስቃሴ ይገደባሉ፤ ከሰው ጋር ማውራት ቶሎ ይሰለቻቸዋል፤ ከወንበር መነሳት ያስጠላቸዋል፤ እንቅልፍ እምቢኝ ይላቸዋል፣ የጎደላቸው ነገር እንዳለም ይሰማቸዋል።
የችግሩ ሰለባ የኾኑ ልጆችን ለማረም ከመሞከር በፊት ግን ወላጆች ራሳቸውን ማረም ተገቢ ነው ባይ ነኝ፤ የችግሩ መንገድ ጠራጊ ወላጆች ናቸውና። ሰላም!
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!