የፖሊዮ ክትባት በየቤት መምጣቱ ሕጻናትን ጠቅሟል።

9
ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን 14 ወረዳዎች የቤት ለቤት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት በዘመቻ እየተሰጠ መኾኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታውቋል።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የክትባቱን ሂደት ምን እንደሚመስል ተሳታፊዎችን በስልክ አነጋግሯል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ የቢሳች ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ አዲሴ አክሎግ የሦስት ዓመት ልጃቸውን አስከትበዋል። የፖሊዮ ክትባቱ በየቤታቸው በመምጣቱም ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውም ገልጸዋል።
በጤና ኬላ ይሰጥ የነበረው ክትባት አሁን ደግሞ ቤት ለቤት መሰጠቱ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ላልተከተቡ ሕጻናት ጠቀሜታ እንዳለው ነው የተናገሩት። በተጓዳኝም ሌሎች የጤና ምክር እና አገልግሎት እየተሰጠ መኾኑንም አንስተዋል።
የቢሳች ቀበሌ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ አተረፍ ውለታው በክትባት ዘመቻው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው እና የቲቪ ምልክቶችን መለየት፣ ጠቃሚ እንክብሎች እና አልሚ ምግብ እደላ፣ የነፍሰ ጡር እናቶች ምዝገባ፣ ተቋርጦ የነበረ ክትባት ማስቀጠል እና ሌሎች የምክር እና ሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ሙላቴ አሻግሬ ለአራት ቀናት በሚቆየው ክትባት ዕድሜያቸው ከአስር ዓመት በታች የኾኑ 941 ሺህ 706 ሕጻናት እንደሚከተቡ ገልጸዋል፡፡
በዘመቻው ክትባት አግኝተው የማያውቁ ሕጻናት እንደሚከተቡ፣ የሥርዓተ ምግብ፣ የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው ሕጻናት፣ የማሕጸን መውጣት ችግር ያለባቸውን እናቶች በመለየት ለሕክምና አገልግሎት እንደሚመቻችም ነው የገለጹት፡፡
በዞኑ በ1ሺህ 459 የክትባት ቡድን፣ 8 ሺህ 745 የጤና ባለሙያዎች እና 7 ሺህ 295 አሥተባባሪዎች እየተሳተፉበት እንደኾነም መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
በዚህ የተቀናጀ የክትባት ዘመቻ ሴቶች እና ሕጻናት እንዲጠቀሙ ባለድርሻ አካላት እና ኅብረተሰቡ ለክትባቱ መሳካት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበዓለም መድረክ ሞገስ ያገኘው የምኒልክ ቴምብር
Next articleየልጅዎን የስልክ አጠቃቀም ይከታተላሉ?