
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ)
የሀገሬው ሰው “ደብዳቤ ቢጽፉት እንደቃል አይኾንም እንገናኝ እና ልንገርሽ ሁሉንም” እያለ ሲቀኝ ኖሯል። ደብዳቤ በአካል እንደመገናኘት ባይኾንም የተራራቁትን በተቻለ መጠን ሲያቀራርብ ኖሯል። የደብዳቤ ማድረሻው ደግሞ ፖስታ ነው።
ሰዎች ደብዳቤውን የሚያደርስላቸውን የፖስታ አገልግሎት ተስማምተው መሠረቱ። የዓለም የፖስታ ድርጅት በዚህ ሳምንት እ.ኤ.አ በ1874 በሲውዘርላንድ ነበር የተመሠረተው።
የዓለም የፖስታ ድርጅት 195 የሚኾኑ አባል ሀገራት አሉት። ከእነዚህ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በ1886 ዓ.ም ነበር በአዋጅ የተቋቋመው። የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ሲነሳ አብሮ የሚነሳው በላዩ ላይ የሚታተመው ቴምብር ይገኝበታል። ይህ ቴምብር ብዙ ነገሮችን የያዘ እና የአንድን ሀገር ገጽታም የሚገልጽ ነው።
ብዙ ሀገራትም ይህንን ቴንብር ያላቸውን ፍላጎት እና ውስጣዊ መሻት ያሳዩበታል። ኢትዮጵያም የፖስታ ድርጅቱ ከተቋቋመ በኋላ የመጀመሪያዎቹ ሰባት ዓይነት ቴምብሮች በፈረንሳይ ታትመው ወደ ሀገር እንዲገቡ አድርጋለች።
ቴምብሮቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ሽያጭ ላይ የዋሉት በ1887 ዓ.ም ነበር። እነዚህ ቴምብሮች ታዲያ የሀገሪቱን ገጽታ እንዲያሳዩ ለማድረግ ብዙ የተደከመባቸው ነበሩ። የመጀመሪያዎቹ አራት ቴምብሮች ዳግማዊ ምኒልክን በዙፋን ልብሳቸው የሚያሳዩ ሲኾን፣ ቀሪዎቹ ሦስቱ ደግሞ የሙዓ አንበሳን ምስል ይዘው ነበር።
የዳግማዊ ምኒልክን በዙፋን ልብሳቸው ኾነው የሚያሳየው ቴንብር ከታተመ ከአንድ ዓመት በኋላ በፓሪስ ከተማ በተዘጋጀው የመጀመሪያው የቴምብር ኤግዚቢሽን ላይ ሲቀርብ ከፍተኛ አድናቆትን ማትረፉ አልቀረም። ምክንያቱ ደግሞ ምልክቱ ብዙ መልዕክት የነበረው ነበርና ብዙዎቹ እንዲወዱት አስገድዷቸዋል።
ኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ የፖስታ ድርጅቱ አባል ባትኾንም በጊዜ ያላት ተቀባይነት እያደገ በመሄዱ በ1901 ዓ.ም የዓለም የፖስታ ኅብረት አባል ኾናለች። ይህ አባልነት የኢትዮጵያ ፖስታ ቴምብሮች የሀገሪቱን ወሰን አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ መሰራጨት እንዲጀምሩ ምክንያትም ኾኗል።
በዚህ አባልነት ምክንያትም የመጀመሪያዎቹ መደበኛ ቴምብሮች በድጋሚ ልዩ ምልክት ታትሞባቸው የመታሰቢያነት ቴምብሮች ኾነው ወጥተዋል።
በ1911 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ በወጡ 15 ዓይነት ቴምብሮች ላይ እንደ ጉማሬ፣ አንበሳ፣ ዝሆን እና ቀጭኔ የመሳሰሉ የዱር እንስሳት ስዕሎች ታትመው ነበር። እነዚህም የመጀመሪያዎቹ የሀገር ውስጥ ሰዓሊያን የሥዕል ሥራ ውጤቶች ነበሩ።
1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ለዳግም ወረራ አዲስ አበባ ሲገባ ቀደም ሲል የታተሙ ቴምብሮች በማቃጠል ታሪክ ለማጥፋት ሞክሯል። እስከ 1933 ዓ.ም ድረስም አዲስ ቴምብር አልታተመም። ጣሊያን ድል ከተደረገ በኋላ በዚሁ ዓመት ሦስት ዓይነት መደበኛ ቴምብሮች ለሽያጭ ቀርበዋል።
በታሪኩ ውስጥ አልፎ አልፎ መቆራረጦች ቢኖሩበትም ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ፖስታ የሀገሪቱን ባሕል፣ ምጣኔ ሃብት፣ ታሪክ፣ ቅርሶች፣ እንስሳት እና ዕፅዋትን የሚያወሱ የተለያዩ መደበኛ እና የመታሰቢያ ቴምብሮችን ሲያትም ቆይቷል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት

የዘንድሮው የዓለም ዕይታ ቀን በዚህ ሳምንት ተከብሯል። ቀኑ እ.ኤ.አ 2000 ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲከበር ሲደረግ ብዙ ምክንያቶች እንደነበሩት ታሪክ ይነግረናል።
የዓለም የዕይታ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ24ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።
ይህ በዓል ሲከበርም ጥሩ ዕይታ አጠቃላይ ደኅንነትን፣ የአካዳሚክ ስኬትን፣ የሥራ ዕድልን እና ኢኮኖሚያዊ ምርታማነትን በእጅጉ ያሳድጋል በሚል ታሳቢ ተደርጎ ነው።
ሀገራት በዜጎቻቸው ላይ የሚደርስን የብረሃን ማጣት እና የዕይታ ችግርን ለመቅረፍ ትኩረት እንዲሰጡ ለማስቻል በዓለም አቀፍ ደረጃ የዕይታ ቀን እየተከበረ ይገኛል።
ይህ በዓል በዚህ ሳምንት እንዲከበር ምክንያት የኾነው ደግሞ ከፍተኛ የዐይን ጤና ችግር ከኾኑት መካከል የዐይን ሞራ ግርዶሽ፣ በመነጽር የሚስተካከል የዕይታ ችግር፣ ትራኮማ እና በስኳር ሕመም ምክንያት የሚመጣ የዐይን ችግርን ለመከላከል ሲባል ነው።
በኢትዮጵያ በዐይን ጤና ዘርፍ በተካሄደው ሀገር አቀፍ ጥናት መሠረት ለዐይነ ስውርነት መንሥኤ ተብለው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል የዐይን ሞራ ግርዶሽ፣ ትራኮማ፣ አጥርቶ የማየት እና የዕይታ አድማስን የሚገድበው ግላኮማ ይገኙበታል።
እስከ 90 በመቶ የሚኾነው የዐይን ጤና ችግር ግን ጉዳት ሳያስከትል መከላከል የሚቻል ለመኾኑ የዓለም ጤና ድርጅት በገጹ ቀኑን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ አስረድቷል።
ሠራተኞች በሥራ ቦታ ለዐይናቸው ጤና ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ እና የሥራ ኀላፊዎችም የሠራተኞቻቸውን የዐይን ጤና በመጠበቅ ምርታማነትን እንዲያሳድጉ የዓለም ጤና ድርጅት ያሳስባል።
ምንጭ፡- ጤና ሚኒስቴር እና የዓለም የጤና ድርጅት

የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ መከበር የጀመረው በዚህ ሳምንት እ.አ.አ 1992 ነው።
ይህም የተጀመረው በዓለም የአዕምሮ ጤና ፌዴሬሽን (World Federation for Mental Health – WFMH) አሥተባባሪነት ነው። ቀኑም ስለ አዕምሮ ጤና ግንዛቤን ማሳደግ ላይ አተኩሮ ነው መከበር የተጀመረው። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በ1994 መሪ ቃል እንዲዘጋጅለት ተደርጎ ተከብሯል።
የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን በዚህ ዓመትም ሲከበር “በድንገተኛ አደጋዎች እና ሰብዓዊ ቀውስ ወቅት የአዕምሮ ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት” በሚል ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ተደርጓል።
የቀኑ ዋና ዓላማ በሰብዓዊ እና ድንገተኛ አደጋዎች (እንደ ተፈጥሮ አደጋዎች፣ ግጭቶች እና ወረርሽኞች) የተጎዱ ሰዎችን የአዕምሮ ጤና እና ሥነ ልቦናዊ ፍላጎት መደገፍ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው።
የአዕምሮ ጤና የግለሰቦች ብቻ ሳይኾን የኅብረተሰብ የጋራ ጉዳይ እንደኾነም የዘርፉ ምሁራን ያብራራሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ በአደጋዎች ወቅት ከ3 እስከ 5 ሰዎች አንዱ የአዕምሮ ጤና ችግር ይገጥመዋል።
በእንዲህ አይነት ቀውሶች ወቅት ከምግብ እና ውኃ በተጨማሪ የአዕምሮ ጤና እና ማኅበራዊ አገልግሎት ለተጎጂዎች ሊቀርብ ይገባል። የአዕምሮ እክል ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃው ስለሚችል ማኅበራዊ ኀላፊነትን ለመወጣት መዘጋጀት እንደሚገባም ነው የሚገለጸው።
የአዕምሮ ጤና ተገቢውን ክብካቤ እንዲያገኝ እና ለተጎዱ ሰዎች ተደራሽ እንዲኾን በተለይም ለሕጻናት፣ ለአረጋውያን እና ለስደተኞች አካታች አገልግሎት ለመስጠት በዘርፉ ላይ ኢንቨስት ማድረግ አስፈላጊ እንደሚኾንም ነው የዓለም የዐዕምሮ ጤና ፌዴሬሽን የሚያሳስበው።
ምንጭ፦ የዓለም የአዕምሮ ጤና ፌዴሬሽን እና ጤና ሚኒስቴር
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!