በክልሉ በትምህርቱ ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት በብዙ ፈተናዎች ያለፈ እና መሻሻል የታየበት ነው።

5

እንጅባራ፡ ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ500 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን የዕውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ2017 የትምህርት ዘመን ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከወሰዱ 6ሺህ 627 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውስጥ 19 ነጥብ 83 በመቶ የሚኾኑት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን ውጤት ሲያስመዘግቡ 30 ተማሪዎችም ከ500 በላይ ከፍተኛ ውጤት አምጥተዋል።

ይህም ባለፈው ዓመት ከነበረው 8 ነጥብ 3 በመቶ የማለፍ ምጣኔ ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ነው ተብሏል።

ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችም የክልል እና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ዕውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታው አለሙ ተማሪዎች በተሻሉ መምህራን እንዲታገዙ በመደረጉ እና አጠቃላይ በትምህርት መዋቅሩ ቅንጅታዊ ሥራ በዚህ ዓመት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

ዘንድሮ የተመዘገበው ውጤት መሻሻል ቢታይበትም አሁንም ከሚጠበቀው በታች ነው ያሉት ኀላፊው በቀጣይ የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር ከዚህ በላይ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞን ለማሳለጥ ያለ ትምህርት የሚታሰብ አለመኾኑን ገልጸዋል። ያደጉ ሀገራት የዕድገታቸው ምስጢር ለትምህርት በሰጡት ትኩረት ልክ እንደኾነም አንስተዋል።

በክልሉ የሚስተዋለው ሕጻናትን ከትምህርት ገበታቸው የማፈናቀል እንቅስቃሴ ዘመን ተሻጋሪ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ያነሱት ምክትል አሥተዳዳሪው እንዲህ አይነት ትውልድ አምካኝ እንቅስቃሴዎችን በጋራ መታገል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደምስ እንድሪስ በዚህ ዓመት በክልሉ የተመዘገበው ውጤት በብዙ ፈተናዎች ያለፈ እና መሻሻል የታየበት መኾኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ውጤት ላበቁ መምህራን፣ አጠቃላይ የትምህርት መዋቅር እና አጋር አካላትም ምሥጋና አቅርበዋል።

በክልሉ አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ያነሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው እነዚህን ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ በጋራ መረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዕውቅና የተሰጣቸው ተማሪዎችም በርካታ መሰናክሎችን አልፈው ለውጤት በመብቃታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል። የተሰጣቸው ዕውቅና ለተሻለ ሥራ እንደሚያነሳሳቸውም ተማሪዎቹ ገልጸዋል።

የዕውቅና መርሐ ግብሩም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ለቀጣይ ዓመት ተፈታኞች ባደረጉት የችቦ ርክክብ ተጠናቅቋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእየተሰጠ ያለው ክትባት ለሕጻናት ጤንነት ትልቅ ፋይዳ አለው።