
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 01 /2818ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከመስከረም 30/2018 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ እየተሰጠ ይገኛል።
በክልሉ በስምንት ዞኖች እና በሪጂዮ ፖሊታንት ከተሞች ነው ክትባቱ እየተሰጠ ያለው። በዘመቻው 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕጻናት ተደራሽ ይኾናሉ ተብሏል። ይህ ክትባት የሕጻናትን ጤንነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ድርሻም አለው።
ክትባቱ ከሚሰጥባቸው አካባቢዎች መካከል የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኝት ቀበሌ 01 ነዋሪ ወይዘሮ መሠረት በሪሁን ከመስከረም 30/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ባለው የፖሊዮ ክትባት ከአንድ ዓመት በታች እና ሰባት ዓመት የኾናቸው ሁለት ልጆቻቸውን እንዳስከተቡ ነግረውናል።
ክትባቱ ከመሰጠቱ በፊት በአካባቢያቸው ባለ የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያ ስለክትባቱ ግንዛቤ እንደተፈጠረላቸው ነው ገልጸዋል። ክትባቱ ለሕጻናቱ ያለውን ጠቀሜታም አውቃለሁ ብለውናል።
ከዚህ በፊትም ለልጆች የሚሰጡ ማንኛውንም ክትባቶች በጤና ባለሙያዎች አማካኝነት እንዲሰጡ ማድረጋቸውን ነግረውናል።
በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የማክሰኝት ጤና ጣቢያ ክላስተር የማክሰኝት 01 ቀበሌ የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያ ጓንሳ መኮነን ደግሞ “ቤት ለቤት በመሄድ እስከ 10 ዓመት ያሉ ሕጻናትን ከዚህ በፊት ቢከተቡም ባይከተቡም እየከተብን ነው” ነው ያሉን።
ሲከትቡ ግን ለወላጆች ለምን እንደሚከተቡ የማስገንዘብ ሥራ እየሠሩ እንደኾነም ባለሙያዋ ጠቁመዋል። እየተሰጠ ያለው ክትባት ሁለት አይነት መድኃኒት ነው የሚሉት ባለሙያዋ ሁለቱም ፖሊዮን ይከላከላሉ ነው ያሉት።
የሚመዘግብ፣ ግንዛቤ የሚፈጥር፣ ቤቶች ላይ ምልክት የሚያደርግ እና ክትባቱን የሚሰጥ ባለሙያ በጋራ በመቀናጀት እየሠሩ መኾኑንም ነግረውናል።
የሰው አቀባበል የተለያየ ቢኾንም ብዙው ማኅበረሰብ የክትባቱን አስፈላጊነት ተገንዝቧል፤ ክትባቱ ከመሰጠቱ በፊት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ ውጤታማ ነውም ብለዋል።
እንደ ማክሰኝት 01 ቀበሌ ለክትባቱ መስጫ የተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ሁሉንም ሕጻናት ተጠቃሚ ለማድረግ ላይበቃ ይችላል ከሚል ስጋት ውጭ የገጠመ ችግር አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር እና የወረርሽኝ በሽታዎች የሥራ ክፍል አሥተባባሪ ዑመር የሻው አሁን የሚሰጠው የፖሊዮ ክትባት ከሌሎች ክትባቶች እንደሚለይ ነግረውናል። የወረርሽኝ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እንደሚባልም ጠቅሰዋል።
በክልሉ ሁለት አካባቢዎች አዲስ የፖሊዮ ቫይረስ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በማሳወቁ ሊዛመት ይችላል ተብለው የተገመቱ ዞኖች ላይ ክትባቱ መሰጠት መጀመሩን ገልጸዋል። የወረርሽኝ ምላሽ የፖሊዮ ክትባት ነው እየተሰጠ ያለው ነው ያሉት።
ክትባቱ ከዚህ በፊት ከአምስት ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት ይሰጥ እንደነበርም አስታውሰዋል። የበሽታ መከላከል አቅምን ለማጠናከር ሲባል እና የመከተብ ዕድል ያላገኙ ልጆች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል ከ10 ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት ክትባቱ እየተሰጠ እንደኾነም አስረድተዋል።
እንደ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከ800ሺህ በላይ ሕጻናትን በክትባቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ነግረውናል። ክትባቱ ከመሰጠቱ በፊት በዘመቻው ለሚሳተፋ ባለሙያዎች ሥልጠናዎች ተሠጥተዋል ነው ያሉት።
ክትባቱ ከሚሰጥበት ጊዜ ቀደም ባሉት አምስት ቀኖችም ለማኅበረሰቡ በየአካባቢው ስለክትባቱ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ800 በላይ ቡድን ተዋቅሮ በዘመቻው እየተሳተፈ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። ለዞኑም በቂ የክትባት መድኃኒት መግባቱን ነግረውናል።
በዞኑ በሚገኙ 15 ወረዳዎች ክትባቱ እየተሰጠ እንደሚገኝም አሥተባባሪው ነግረውናል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!