ሕጻናት የፖሊዮ ክትባትን በአግባቡ እንዲወስዱ ማኅበረሰቡ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ።

2

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ከሰው ወደ ሰው በቫይረስ አማካኝነት የሚተላለፍ በሽታ ነው። ቫይረሱ የነርቭ ሥርዓትን በማጥቃት ለአካል ጉዳት እንደሚዳርግ እና በክትባት መከላከል እንደሚቻል የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

አሚኮ ያነጋገራቸው የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ከድጃ ማሩ የሁለት ዓመት ከስድስት ወር ልጃቸውን ከፖሊዮ ለመታደግ ወደ ክትባት መስጫ ጣቢያ መሄዳቸውን ተናግረዋል።

ወይዘሮ ከድጃ ከዚህ በፊትም ከተለያዩ በሽታዎች የሚከላከል ክትባት በመንግሥት ሲሰጥ ልጆቻቸውን እንደሚያስከትቡ እና ዛሬም ልጃቸው የፖሊዮ ተጠቂ እንዳይኾን ማስከተባቸውን ተናግረዋል።

ማንኛዋም እናት ልጆቿን በማስከተብ የሚጠበቅባትን የእናትነት ድርሻ ልትወጣ ይገባል ነው ያሉት።

የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር የፖሊዮ ክትባት አስተባባሪ ደስታው ከፍያለው ክትባቱ ከመጀመሩ በፊት በክልል ደረጃ ሥልጠና በመውሰድ ክትባት የሚሰጡ ባለሙያዎችን እና የሚመለከታቸውን አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።

ከመስከረም 30/2018 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የከተማ እና የገጠር ቀበሌዎች ለተከታታይ አራት ቀናት ክትባቱን ለመስጠት ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል።

የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ በረከት ደገፋው ማኅበረሰቡ ልጆቹን ለማስከተብ ያሳየው ፍላጎት ጥሩ ነው ብለዋል።

የፖልዮ ክትባቱን ለመስጠት የተሟላ ግብዓት እና የሰው ኀይል በመያዝ ወደ ሥራ እንደተገባም አስታውቀዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ ከ37ሺህ በላይ ሕጻናትን የፖሊዮ ክትባት ለመከተብ ታቅዶ ወደ ሥራ እንደተገባም አብራርተዋል።

ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት በአግባቡ እንዲወስዱ ማኅበረሰቡ ኀላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ኀላፊው አሳስበዋል።

የፖሊዮ ክትባት በዋናነት ቤት ለቤት፣ በትምህርት ቤቶች እና ሕጻናት ሊገኙ በሚችሉበት ቦታ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት አገልግሎትን ካላገኙ የበሽታ መከላከል አቅማቸው ስለሚዳከም ለተለያዩ ጉዳቶች እንደሚዳረጉ ታውቆ ለክትባቱ ትኩረት እንዲሰጥም አስገንዝበዋል።

ከመስከረም 30/2018 ጀምሮ እየተሰጠ ባለው የፖሊዮ ክትባት መከተብ ያለባቸው ሕጻናት ክትባቱን እንዲወስዱ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ:-ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ የወላጆች ሚና ከፍተኛ ነው።
Next articleእየተሰጠ ያለው ክትባት ለሕጻናት ጤንነት ትልቅ ፋይዳ አለው።