
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ስር ካሉ ትምህርት ቤቶች በ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ፈተናዎች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ተማሪ ሰላማዊት አያልነው በመርሐ ግብሩ አንዷ ተሸላሚ ኾና ነው ያገኘናት። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጅነሪንግ እና ሒሳብ ማበልጸጊያ (ስቲም)ማዕከል ትምህርቷን ስትከታተል ቆይታ የ12ኛ ክፍል ፈተና 550 ነጥብ 8 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች።
ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት በክፍል ውስጥ የሚሰጣትን ትምህርት በአግባቡ በመከታተል ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀሟ ለከፍተኛ ውጤት እንዳበቃት ትናገራለች።
ተማሪ ሰላማዊት እንደገለጸችው ፈተና ከመጀመሩ በፊትም የጥናት መርሐ ግብር አውጥታ ሰፊ ጊዜ ለንባብ ሰጥታ በመዘጋጀቷ ውጤታማ እንድትኾን አድርጓታል። በቀጣይም ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በጤና ዘርፍ የሕክምና ትምህርቷን እንደምትቀጥል ተናግራለች።
በእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ ያገኘናት ተማሪ ታሪክ ደሳለኝ የ8ኛ ክፍል ፈተናን 94 ነጥብ 7 አማካይ ውጤት ማምጣቷን ትናገራለች።
ተማሪ ታሪክ እንደገለጸችው በክፍል ውስጥ የሚሰጡ ትምህርቶችን በንቃት በመከታተል፣ ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር በመረዳዳትና በግል በማጥናቷ ጥሩ ውጤት እንድታስመዘግብ አግዟታል። ውጤታማ ኾና ዛሬ ላይ ለሽልማት በመብቃቷም ደስታን እንደፈጠረላት ነው የገለጸችው።
በቀጣዩ የትምህርት ሂደትም ፈጠራ ላይ ባተኮረ የመማር ሂደት እንደምትቀጥልና የ12ኛ ክፍል ፈተናን በከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት እንደምትፈልግ ገልጻለች።
በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትምህርቷን በመከታተልም አውሮፕላን አብራሪ የመኾን ራዕይ እንዳላትም ነግራናለች።
ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ የወላጆች ሚና ከፍተኛ ነው የሚሉት ደግሞ የተማሪ ታሪክ ወላጅ አባት ደሳለኝ ታዬ ናቸው። ልጃቸው ውጤታማ ኾና ስትሸለም በማየታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
በቤተሰብ ደረጃ የሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉላት እንደኾነም ገልጸዋል። ወላጆች ካለን ጊዜ ለቤተሰብ የምንሰጠው እና ልጆችን የምንከታተልበት በቂ ጊዜ ልንሰጥ ይገባል ይላሉ።
በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲኾኑም ማበረታታት እና የሚፈልጉትን የመማሪያ ቁሳቁስ ማሟላት እንደሚያስፈልግ ሀሳባቸውን አጋርተውናል።
አቶ ደሳለኝ ልጆች የወላጆችን የቅርብ ክትትል ይፈልጋሉ ብለዋል። የቤተሰብ ፍቅር መሥጠት፣ ሲማሩ የዋሉትን ትምህርት መጠየቅ፣ የተሰጡትን የቤት ሥራዎች መጠየቅ እና ስለ ትምህርት ቤት ውሏቸው መከታተል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!