“በጠብታ ደም ሕይወት መታደግን ባሕል ልናደርግ ይገባል” ደም ለጋሾች

7

ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ባንክ ታላቅ ሀገር አቀፍ የደም ልገሳ መርሐ ግብርን በተለያዩ ከተሞች እያካሄደ ነው።

ወጣት ዘነቡ ካሳዬ የደብረ ብርሃን ከተማ ወጣት ነች። ከሰባት ዓመት በፊት እናቷ በወሊድ ወቅት የደም እጦት አጋጥሟት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሽ በተሰጣት ደም ሕይወቷ መትረፉን እና ልጇን መታቀፍ መቻሏን አስታውሳናለች።
ይህ አጋጣሚ ደም ለመለገስ እንዳነሳሳት የምትናገረው ወጣት ዘነቡ ደም መለገስ የሰውን ሕይወት መታደግ ነው ትላለች። ደም መለገስ በቃላት የማይገለጽ እርካታን ይሰጠኛል ነው ያለችው።

የዓባይ ባንክ 15ኛ ዓመት ምስረታን አስመልክቶ በደብረ ብርሃን ከተማ ዲስትሪክት በተካሄደ የደም ልገሣ ላይ ነው ወጣቷ ደም ስትለግስ አግኝተናት ይህን ያለችን።

በተመሳሳይ ደም ሲለግስ ያገኘነው የዓባይ ባንክ ባለሙያ አሸብር አደናግ የማይተካውን የሰው ሕይወት በሚተካ የደም ጠብታ ለመታደግ በማለም ደም መለገሱን ተናግሯል፡፡

የዓባይ ባንክ ደብረ ብርሃን ዲስትሪክት የሃብት ማሠባሠብ ክፍል ሥራ አሥኪያጅ ፍቅሬ ነጋሽ ደም የመለገስ ባሕላችን ዝቅተኛ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ደም የሚፈልጉ ወገኖቻችን ብዙ በመኾናቸው ዓባይ ባንክ 15ኛ ዓመቱን በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ በመኾኑ የደም ልገሳ መርሐ ግብሩም በሁሉም የባንኩ ዲስትሪክቶች እና ቅርንጫፎች እየተካሄደ ስለመኾኑ ገልጸዋል።

“ጠብታ ደም የሰው ሕይወትን ታድናለችና ደም መለገስ ባሕላችን ልናደርግ ይገባልም” ብለዋል፡፡ ዓባይ ባንክ ይሄንኑ ተግባር በማጠናከር ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እንደሚወጣም ተናግረዋል።

የዲስትሪክቱ የኦፕሬሽን እና ሠው ኃይል አሥተዳደር ሥራ አሥኪያጅ በየነ አየለ ባንኩ በአረንጓዴ አሻራ፣ በተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እና መሰል የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

546 ቅርንጫፎች በአንድ ልብ ደም በመለገስ ውድ እና ክቡር የሰው ሕይወትን እንታደግ በሚል መርሕ የባንኩ ሠራተኞች እና ደንበኞች በዛሬው ዕለት የደም ልገሳ እያከናወኑ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።

በ2018 የበጀት ዓመት 9ሺህ 500 የደም ዩኒቶችን ለማሠባሠብ መታቀዱን የገለጹት የደብረ ብርሃን ደም ባንክ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ በዛብህ ዓባይነህ ናቸው። ባለፉት ሦስት ወራት 3ሺህ 883 ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኛ ለጋሾች ማሠባሠብ ተችሏል ብለዋል።

አገልግሎቱ ለ17 የጤና ተቋማት ደም እንደሚያቀርቡ የተናገሩት አቶ በዛብህ ዓባይ ባንክ ዛሬ ሠራተኞቹን እና ደንበኞቹን በማስተባበር እያካሄደ ያለዉ መልካም ተግባር በሌሎች ተቋማትም ሊለመድ ይገባል ነው ያሉት።

ዓባይ ባንክ ደብረ ብርሃን ዲስትሪክት በዛሬው የደም ልገሳ መርሐ ግብር 60 ዩኒት ደም ለማሠባሠብ ሰለማቀዱም ተመላክቷል።

ዘጋቢ:- ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአካል ጉዳተኞች መብታቸውን እና ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ ማኅበረሰቡ ድጋፍ ማድረግ አለበት።
Next articleተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ የወላጆች ሚና ከፍተኛ ነው።