አካል ጉዳተኞች መብታቸውን እና ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ ማኅበረሰቡ ድጋፍ ማድረግ አለበት።

3

ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 ዓ.ም የተመሠረተው የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን 400 ወንድ እና 300 ሴት አካል ጉዳተኞችን በውስጡ ይዟል።

የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ኅላፊ ታከለ ቢሆን “ኹኔታዎች ከተመቻቹልን ማንኛዉም ጉዳቱ የሌለበት ሰው የሚሠራውን ሥራ መሥራት እንችላለን” ብለዋል ።

የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አላማው የተደበቁ አካል ጉዳተኞችን አደባባይ ማውጣት መኾኑንም ገልጸዋል።

አካል ጉዳተኞች መብታቸውን እና ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ ማኅበረሰቡ ልዩ ድጋፍ ማድረግ አለበት ያሉት ኅላፊው የቦታ አለመመቻቸት ነው እንጂ አካል ጉዳተኞች ጉዳት አልባ ከኾነው ሰው አንለይም ብለዋል።

የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የራሱ የኾነ ቢሮ፣ መሠብሰቢያ አዳራሽ እና መገልገያ ቁሳቁስ እንዳልነበረውም ተገልጿል።

አሁን ግን የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጋር በጋራ በመኾን ቢሮ ሠርቶ አስረክቦናል፣ የቁሳቁስ ድጋፍም አድርገውልናል ብለዋል።

የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ የልፍኝ በላቸዉ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ተግባር መሥራት ላይ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ኅላፊነት አለበት ነው ያሉት።

መንግሥትም ግለሰብም አካል ጉዳተኞች የብዙ ዕውቀት ምንጭ መኾናቸውን በመገንዘብ እና እነሱን አካቶ በመሥራት ኅላፊነትን መወጣት ይገባል ብለዋል።

አካቶ ትግበራ ላይ ከአካል ጉዳተኞች ጋር በጋራ እየሠራን ነው ያሉት ኅላፊዋ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የአንድ መሥሪያ ቤት ጉዳይ ብቻ አለመኾኑንም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በደሴ ከተማ የአንድ ሚሊዮን የበሽ ጥቅል አገልግሎት አሸናፊ ሽልማቱን አስረከበ፡፡
Next article“በጠብታ ደም ሕይወት መታደግን ባሕል ልናደርግ ይገባል” ደም ለጋሾች