
ደሴ: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ መልዕክት 46ኛው የዓለም ቱሪዝም ቀን በደሴ ከተማ ተከብሯል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ ተሳታፊዎች የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ በትብብር መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል። በተለይ ሕጻናት እና ወጣቶችን በቱሪዝም ክበባት እንዲሳተፉ በማድረግ ዘርፉን ማነቃቃት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ትዕግስት አበበ ደሴ ከተማ በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ባለቤት ናት ብለዋል።
እነዚህን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በመመዝገብ እና በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ሰይድ የሱፍ ከተማ አሥተዳደሩ ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
ታሪካዊ ቦታዎችን በመጠበቅ እና በማልማት ለቱሪስቶች ምቹ የማድረግ ሥራ ይከናወናል ብለዋል። ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች በመገንባትም ለቱሪስቶች ምቹ ኹኔታን ለመፍጠር ይሠራል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሰይድ አብዱ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!