“ጎንደር የከፍታ ደረጃዋን ግርማ ሞገስ ተላብሳለች” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)

8

ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች በጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እምዬ ጎንደር የአይቻልም አስተሳሰብ የመከነባት፣ አስተዋይነትና አብሮነት ያሸነፈባት ናት ብለዋል።

ጎንደር የከፍታ ደረጃዋን ግርማ ሞገስ ተላብሳለች ያሉት ኀላፊው ሙሽራዋ እምዬ ጎንደር አሁን ገፅታዋም ሳቢና ማራኪ ኾኗል ነው ያሉት። ከነበሩባት ችግሮች ተስፈንጥራ በመውጣት ታሪካዊና ዘመን ተሻጋሪ የልማት ውጤቶችን እየሠራች መኾኗን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የጎንደር ምልከታችን የትናቱን፣ የአሁኑን እና የተሻለ ነገን ተስፋ አንድ ላይ የሚያጣምር ነው ብለዋል።

በአካባቢዎቹ የትኛውም አይነት ሕዛባዊም ይሁን መንግሥታዊ አገልግሎት ሳይቋረጥ ፕሮጀክቶችን መፈጸም ፈታኝ ቢኾንም ጎንደሮች የሥራ ባሕላቸውን ቀይረው፣ በአርቆ ማየት፣ በአዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦች አሳክተውታል ነው ያሉት።

የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች አዳዲስ ፕሮጀክቶች እና የነበረቱን በማደስ ሂደት ያሉ ፕሮጀክቶች በፍጥነት የሚጠናቀቁበትን ኹኔታ ቀይሰው እየሠሩ መኾናቸውን መመልክታቸውንም አንስተዋል።

ታሪካዊና ዘመን ተሸጋሪ ልማት ከግብ እንዲደርስ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሁሉ፣ የከተማው ቁርጠኛ መሪዎች እና ባለሙያዎችን አመስግነዋል። እንዲበረቱም አሳስበዋል።

ሰላምን በማፅናት፣ ፈጣን ልማት በማከናወን የሕዝባችንን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለሀገራችን ከፍታ የምንተጋበት ዓመት ነው ያሉት ኀላፊው በጎንደር ከተማ በርካታ አበራታች ለውጦች ተመልክተናል፤ የሚቀሩ ተግባራትን አጠናክረው በመሄድ በላቀ ሁኔታ እንዲፈፅሙ አደራ እላለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው።
Next articleየቱሪዝም ሃብቶችን በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሠራ ነው።