ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው።

3

ጎንደር: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በጥራጥሬ እና ቅባት እህል ዘርፍ የውጭ ንግድን ለማሳደግ በሚያስችል ኹኔታ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) ውይይቱ በ2017/18 የምርት ዘመን የለሙ ሰብሎችን ከአምራች እስከ ውጭ ገበያ አቅራቢዎች ድረስ የግብይት ሰንሰለት ድረስ በማገዝ ውጤታማ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር ያለመ መኾኑን ተናግረዋል።

በምርት ዘመኑ በግብይት ሥርዓት ላይ በተለይም በትራንስፖርት እንቅስቃሴ የሚያጋጥመውን የጸጥታ ችግር በትብብር ለመፍታት የሚያስችል ውይይት እንደኾነም ነው የገለጹት።

በ2017/18 የምርት ዘመን በአኩሪ አተር 325 ሺህ፤ በሰሊጥ 548 ሺህ፤ በማሾ 55 ሺህ እና በቦለቄ 96 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል መልማቱን ተናግረዋል። በአማራ ክልል የቅባት እህል እና የጥራጥሬ ምርት እያደገ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በ2017 ዓ.ም በሰሊጥ፣ በቦለቄ፣ በማሾ እና በአኩሪ አተር 6 ሚሊዮን 964 ሺህ 426 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደተቻለ ነው የተናገሩት። የቅባት እና የጥራጥሬ ምርት እና ግብይት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በላኪዎች፤ በውል እርሻ፤ በአቅራቢ ነጋዴዎች እና በአምራች ፋብሪካዎች አማካኝነት ለግብይቱ አማራጭ የገበያ ሥርዓቶች መዘርጋታቸውን ኀላፊው ጠቁመዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል እና ለሀገር ውስጥ ኢንዳስትሪዎች ደግሞ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርትን ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑንም ዶክተር ኢብራሂም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት የጥራጥሬ እና የቅባት ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሀገር ደረጃ ቀዳሚ መኾኑንም ጠቁመዋል። የግብይት ሥርዓቱ ከሕዳር አንድ ጀምሮ እንደሚካሄድም አብራርተዋል።

በወረዳ ደረጃ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲያግዝ ይሰጥ የነበረውን ሸኝ ደብዳቤ ወደ ክልል በማምጣት ሕገ ወጥ ንግድን ለማስቀረት አዲስ አሠራር መቀመጡንም ቢሮ ላፊው ጠቁመዋል።

ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን በመቆጣጠር የንግድ ሥርዓቱን የሚያደናቅፉ የትራንስፖርት ችግሮችን ለመቅረፍ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም በዕለቱ ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ አቅራቢዎች በበኩላቸው የግብይት ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ ያለው ተግባር አበረታች መኾኑን አንስተዋል። ምርትን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የሚያጋጥመውን የጸጥታ ችግር በመቅረፍ በኩል መንግሥት በትኩረት እንዲሠራም ጠይቀዋል።

በዘንድሮው ዓመትም “ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ ለማቅረብ እንደሚሠሩ”ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኮምቦልቻን በኢንደስትሪ ተመራጭ ለማድረግ ይሠራል።
Next article“ጎንደር የከፍታ ደረጃዋን ግርማ ሞገስ ተላብሳለች” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)