
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂደዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ የጤና ልማት እቅዶች ተነድፈው ሲተገበሩ ቆይተዋል ብለዋል።
በተለይም ደግሞ “በሚሊኒየም የልማት ግብ” መርሐ ግብር የተላላፊ በሽታዎችን ጫና መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት። የእናቶችን እና የሕጻናትን ጤና አገልግሎት በማሻሻል ይደርስ የነበረውን ሞት መቀነስ መቻሉንም በአብነት አንስተዋል።
ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ባለፈ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች የሃሳብ እና የሃብት ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ላይም ከመከላከል ባለፈ አክሞ ማዳን ላይ ትኩረት ተደርጎ እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በቀጣይ የክልሉን ሕዝብ ጤና ለማሻሻል የ25 ዓመታት የጤና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በክልሉ በጤናው ዘርፍ የታቀደው አሻጋሪ ዕቅድ ውጤታማ እንዲኾን አጋር አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። “የማኅበረሰቡን ጤና ማሻሻል ላይ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባልም” ብለዋል።
የአምረፍ ሄልዝ አፍሪካ የአማራ ክልል ሪጅናል ማናጀር ደሴ ካሳ ድርጅቱ በክልሉ የእናቶችን፣ ሕጻናት እና የወጣቶች ጤና ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የሕክምና መሳሪያዎችን በመደገፍ እና በዲጂታላይዜሽን ሥራ የጤና ተቋማትን የማጠናከር ሥራ እየሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል። ድርጅቱ ከጤና ተቋማት ባለፈ ትምህርት፣ ሴቶች እና ተፈናቃዮች ላይ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የጤና ልማት እና ጸረ ወባ ማኅበር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አክሊሉ ጌትነት ማኅበሩ በ2017 ዓ.ም የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል። በጤና ዘርፍም ከ600 በላይ ለሚኾኑ የጤና ተቋማት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግሥት መሠረታዊ ሕይወት አድን የጤና ግብዓቶችን የማጓጓዝ ሥራ ሠርቷል ነው ያሉት።
ግብዓቱ ከ6 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚኾን እንደኾነም ገልጸዋል።
በዚህ ሳምንት ብቻ ከ100 በላይ ለሚኾኑ የጤና ተቋማት ግብዓቶችን የማከፋፈል ሥራ አየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በዕለቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የጤና ቢሮ እድሳትን ጎብኝተዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!