
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የ12ኛ እና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የእውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው “ትምህርት ዋናው የሥልጣኔ ምንጭ ነው” ብለዋል። ሀገራት ለትምህርት በሰጡት ቦታ ልክ ዓለምን ለመቀየር የሚያስችል የፈጠራ እና የምርምር ባለቤት መኾናቸውን አንስተዋል።
እንደ ሀገርም ለችግሮቻችን መፍትሔ የሚኾነው ትምህርት መኾኑን ገልጸዋል። ሀገር የሚገነባው በትምህርት እንደኾነ ነው የገለጹት። ትውልዱ በዕውቀት ሊገነባ፣ በትምህርት ሊበለጽግ ይገባል ነው ያሉት።
የከተማ አሥተዳደሩ ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ልዩ ክትትል እንደሚደረግ አመላክተዋል።
የዛሬው እውቅና ዓላማው እስከ አሁን ለመጣችሁበት ጉዞ በርቱ ለማለት ነው ብለዋል። ለቀጣይ ሕይወታቸው ጠንክረው እንዲማሩ እና ተምረው ለወገኖቻቸው አለኝታ እንዲኾኑ ኀላፊነት እና አደራ የተሰጠበት ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።
የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ድጋፍ ላደረጉ እና የከተማ አሥተዳደሩ አርዓያ ለኾኑት ወላጆችም ምስጋና አቅርበዋል።
ከባሕር ዳር ከተማ ውጭ ያሉት ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ሁሉም ሚናውን መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ምሪያ ኀላፊ ሙሉ አለም አቤ(ዶ.ር) በ2017 ዓ.ም ያጋጠሙንን ችግሮች በመቋቋም ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
የዛሬ ተማሪዎች፣ የነገ ሀገር ተረካቢዎች ውጤታችሁ ለዛሬ ብቻ ሳይኾን ለነገ የሕይወት ጉዟችሁ የሚኾን የመሠረት ድንጋይ አስቀምጣችኋል ነው ያሉት። ይህንን እንደ መጀመሪያ ወስዳችሁ ለቀጣይ የትምህርት ሕይወት በራሳችሁ የምትጓዙበት ነው ብለዋል።
መምህራን አስተማሪ ብቻ አይደሉም፣ የለውጥ ኃይሎች ጭምር ናቸው ብለዋል። የድህነት መንገድ መውጫ መንገድ መኾኑን በማስተማር እና በመቅረጽ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱም ነው የተናገሩት። የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ተማሪ መልዕክተ ዩሐንስ በ12ኛ ክፍል ፈተና 543 በማምጣት በዛሬው ዕለት እውቅና ከተሰጣቸው ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት። ተማሪ መልዕክተ ባገኘችው ሽልማት እና እውቅና መደሰቷን ገልጻለች።
በርትታ በማጥናቷ ለተሻለ ውጤት መብቃቷን የገለጸችው ተማሪ መልዕክተ ከፍተኛ ውጤት ለመምጣቱ የወላጆቿ እና የመምህራን ድጋፍ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አንስታለች።
በቀጣይም የኮምፒዩተር ሳይንስ በማጥናት በቴክኖሎጅ ዘርፍ ትምህርቷን መቀጠል እንደምትፈልግ ገልጻለች።
በዛሬው ዕለት እውቅና የተሰጣቸው በ12 ኛ ክፍል ፈተና ከ500 በላይ ያመጡ 106 ተማሪዎች እና በ8ኛ ክፍል ፈተና ከ94 በላይ አማካይ ውጤት ያመጡ 17 ተማሪዎች ናቸው።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!