
አዲስ አበባ: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ባንክ ታላቅ ሀገር አቀፍ የደም ልገሳ መርሐ ግብርን በአዲስ አበባ ከተማ አስጀምሯል።
15ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ የሚገኘው ዓባይ ባንክ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በመወጣት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የሚተገበር ሀገር አቀፍ የደም ልገሳ ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል።
የደም ልገሳ እያደረጉ ያገኘናቸው የባንኩ ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች ዓባይ ባንክ የደም ልገሳ መርሐ ግብር ማዘጋጀቱ ለማኅበራዊ ግልጋሎት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
ደም ያስተሳስራል፤ አንድም ያደርጋልና እኛም ደም በመለገሳችን ደስተኞች ነን ብለዋል። ሁሉም አቅሙ የቻለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል።
የዓባይ ባንክ የስትራቴጂ ዋና መኮንን ወንድይፍራው ታደሰ የደም ልገሳ ሂደቱ በመርሐ ግብሩ ከሚሳተፈው የደም ለጋሽ ብዛት አንጻር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ደም መለገስ ከሁሉም የላቀ የሕይወት ስጦታ ነው፤ ዓባይ ባንክም ሕይወትን በማዳን ይበልጥ ያደምቃታል፤ ያስቀጥላታል፤ ይህንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በዋናው ዲስትሪክቱ ከሚገኙ ሠራተኞች፣ ከደንበኞች እና ከመላው የባንኩ ሠራተኞች የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን በማንቀሳቀስ ለከፍተኛ የሕይወት አድን አላማ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የበጎ አድራጎት ሥራው የባንኩን የ15 ዓመት ጉዞ በድምቀት ለማክበር እና ማኅበራዊ ኀላፊነትን በመወጣት ረገድ የጎላ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል።
የደም ልገሳ መርሐ ግብሩም በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች እንደሚቀጥል ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!