
አዲስ አበባ: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዘመን ባንክ አክሲዮን ማኅበር የባለ አክሲዮኖች 17ኛ ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤ እና 12ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዷል።
የባንኩን የባለፈው ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የዘመን ባንክ አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሠብሳቢ እንዬ ቢምር ባንኩ በዓመቱ የላቀ አፈጻጸም ነበረው ብለዋል። ለዚህ ስኬትም የደንበኞች፣ የሠራተኞች እና የባለ አክሲዮኖች ጥረት መልካም እንደነበር አንስተዋል።
እንደ ሀገር የተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የብሔራዊ ባንክ አዋጆች መሻሻል፣ የውጭ ኢንቨስትመንት መነቃቃት እና የውጭ ምንዛሬ ፍሰት መጨመር ሚናቸው ከፍ ያለ እንደነበርም ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ 14 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ማግኘት እንደቻለ የገለጹት የቦርድ ሠብሳቢዋ ከዚህ ውስጥ “5 ነጥብ 8 ቢሊዮን የተጣራ ትርፍ ነው” ብለዋል።
ባንኩ ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ በመበጀትም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ስለመሳተፉም ተገልጿል።
ባንኩ ከባንክ ኢንዱስትሪ ተግባሩ ባሻገር ተቋማዊ ማኅበራዊ ኀላፊነቱንም ስለመወጣቱ የቦርድ ሠብሳቢዋ ተናግረዋል። በዚህም ከ61 ሚሊዮን በላይ ብር ወጭ አድርጓል ነው ያሉት። ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎትም ዲጂታል አሠራርን በሰፊው ተግብሯል ብለዋል።
አሁን ላይ የዘመን ባንክ ጠቅላላ የሃብት መጠን 88 ቢሊዮን ብር በላይ ሲኾን ከዚህ ውስጥ ከ64 ቢሊዮን ብር በላይ የሚኾነው ተቀማጭ ነው ብለዋል። ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታልም አስመዝግቧል ነው ያሉት።
ከ41 ቢሊዮን በላይ ብርም ለብድር አገልግሎት ሰጥቷል ብለዋል ሰብሳቢዋ። ዘመን ባንክ በቀጣይ የካፒታል መጠንን ለማሳደግ፣ የዲጂታል ሽግግርን ለመተግበር፣ ፈጠራን ከዲጂታል አገልግሎት ጋር በማቀናጀት በመሥራት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እና አገልግሎቱን ለማሳደግ እንደሚሠራም በዕለቱ ተገልጿል።
ባንኩ በጉባዔው ላይ ከባለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸሙ ሪፖርት በተጨማሪ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
ዘጋቢ:- አዲሱ ዳዊት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!