
አዲስ አበባ: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ የሚከበረው የሳይበር ደኅንነት ወር ዛሬ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አገልግሎት ተከፍቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጸሕፈት ቤት ኀላፊ እና የካቢኒ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ የሳይበር ዘርፉ ተገላጭነት እና ስጋት ያለበት በመኾኑ ከሉዓላዊነት ጉዳይ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም ብለዋል።
ለሳይበር ደኅንነት ችግር እና ጥቃት ምክንያቱ የግንዛቤ ማጠር መኾኑን ያነሱት ሚኒስትሯ በአሁኑ ሰዓት 50 ሚሊዮን ዜጎች ኢንተርኔት የሚጠቀሙ በመኾኑ ይህ ሁሉ ስለ ደኅንነት ግንዛቤ ከሌለው ተጋላጭነትን ከፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
ይህንን ግንዛቤ የመፍጠር እና የማሳደግ ሥራ በዋናነት በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አገልግሎት ይጀምር እንጂ ሌሎች የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች እና መገናኛ ብዙኃን ኀላፊነት አለባቸው ብለዋል።
የሳይበር ደኅንነት ለዲጅታል ኢትዮጵያ መሳላጥ ወሳኝ መኾኑንም አንስተዋል። ምክንያቱ ደግሞ ሀገራዊ የተቋማት እና ትግበራዎቻችን ወደ ድጅታል አሠራር በመግባታቸው ነው ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ የሳይበር ደኅንነት ወር መከበር ዋና ዓላማ ሀገራት ለዜጎቻቸው እና ለተቋማቶቻቸው የሳይበር ደኅንነት ግንዛቤን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮችን ለማከናወን ነው ብለዋል።
በዕለቱ ሀሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መከላከል ላይ መሠረት ያደረረገ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ:- አንዷለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!