ኮሌጆች የአካባቢውን ጸጋ ለይተው በመሥራት ማሳያ እየኾኑ ነው።

1

ፍኖተ ሰላም: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፍኖተ ዳሞት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከመማር ማስተማር ተግባራት ባለፈ በእንስሳት እርባታ እና በሰብል ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።

ኮሌጁ በመደበኛው እና በአጫጭር ኮርሶች ሥልጠናዎችን በመስጠት የተሻለ የሰው ኀይል እያፈራ ነው።

ኮሌጁ ከሥልጠና ባሻገር በሰብል ልማት የበቆሎ እና የስንዴ ሰብልን በማዝመር ለሠርቶ ማሳያ እና ለማስተማሪያ አገልግሎት እያዋለ መኾኑን በፍኖተ ዳሞት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሰብል ልማት አሠልጣኝ መምህሩ አስማረ ካሴ ተናግረዋል።

የሰብል ልማቱ ኮሌጁ ላይ ያሉ ሠልጣኞች ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር በተግባር ትምህርት ብቁ ኾነው እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል። የተሻሻለ የእንስሳት እርባታ ላይም ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል። ዝርያቸው የሻሻሉ የወተት ላሞችን በማርባት ጥሩ ምርት ለማግኘት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።

ተደራጅተው ወደ ሥራ ለሚገቡ ሥራ ፈጣሪዎች አጫጭር ሥልጠና በመስጠት ትርፋማ እንዲኾኑ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ነው ያሉት። ለአካባቢው ማኅበረሰብ ወተት በዝቅተኛ ዋጋ እያቀረቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

በኮሌጁ ውስጥ ወተት ለመግዛት መጥተው ያገኘናቸው አስተያየት ሰጭዎችም አንድ ሊትር ወተት በ50 ብር በመግዛት ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል። በዝቅተኛ ዋጋ ከመግዛት ባሻገር ጥራት ያለው ወተት ማግኘታቸውንም አንስተዋል።

የፍኖተ ዳሞት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አንተነህ ባሕሩ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ መደበኛ ሠልጣኞችን እና አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት ብቁ የሰው ኀይል በማፍራት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ተገቢ አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ተናግረዋል።

ከመደበኛው መማር ማስተማር በተጨማሪ በእንስሳት እርባታ እና ሰብል ልማት ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን እየተሠሩ ያሉ የወተት ልማት ሥራዎችን ወደ ዘመናዊ አሠራር በማሸጋገር የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

በከተማ ግብርና ላይም ተሳትፎ በማድረግ በአትክልት እና ፍራፍሬ ተግባራት ላይ በመሥራት የአካባቢው ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ አያሌው ያረጋል ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን በሙያ በማሠልጠን ብቁ የሰው ኃይል እያፈሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ ካሉ የሙያ እና ቴክኒክ ኮሌጆች የፍኖተ ዳሞት እና ቡሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የአካባቢውን ጸጋ በመለየት ገቢ በማስገኘት እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ለሠርቶ ማሳያነት በማቅረብ ኅብረተሰብ እያገለገሉ ነው ብለዋል።

ኮሌጆች የአካባቢውን ጸጋ ለይተው በመሥራት ማሳያ እየኾኑ እንደኾነም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ መከላከል ይገባል።
Next articleየሳይበር ደኅንነት ከሉዓላዊነት ጉዳይ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም።