
ገንዳ ውኃ: ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ ከ56 ሺህ 800 በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች በወባ ወረርሽኝ በሽታ መያዛቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል።
በአማራ ክልል የወባ ወረርሽኝ በሽታ በስፋት ከሚሠራጭባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የምዕራብ ጎንደር ዞን ነው። የወባ ወሽታ ሲከሰት በአቅራቢያው በሚገኝ የጤና ተቋም ሂደው ካልታከሙት አደገኛ እና ለሞት የሚያበቃ በሽታ ነው።
አቶ ከድር ሙሐመድ የመተማ ዮሐንስ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በወባ በሽታ ሁልጊዜ እንደሚታመሙ ገልጸዋል። ከልጅነታቸው ጀምሮ ወባ እንደሚያማቸው እና በተደጋጋሚ እንደምትነሳባቸው ነው የተናገሩት።
በሚኖሩበት አካባቢ የታቆሩ ውኃዎች እንዳልተፋሰሱ፣ አጎበር እንዳልተሰራጨ እና ደረቅ ቆሻሻዎች እንደሚበዙ ገልጸዋል። በአካባቢያቸውም በብዛት ሕጻናት እንደሚታመሙ ነው የተናገሩት።
ሲያማቸውም ወደ ጤና ጣቢያ በመሄድ የሕክምና አገልግሎት እንዳገኙ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደምም የሚታዘዝላቸውን መድኃኒት ትንሽ ቀን ወስደው ሲያስታግስላቸው አቋርጠው ይተውት እንደነበር የተናገሩት አቶ ከድር አሁን ግን የታዘዘላቸውን መድኃኒት በአግባቡ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
አቶ ጥላሁን አባተ እና ወጣት ትዕግስት ደጀን የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። ማኅበረሰቡ በአካባቢው ያለውን ደረቅ ቆሻሻ ባለማቃጠል፣ ሳሮችን ባለማጨድ እና የታቆረውን ውኃ ባለማፋሰስ ምክንያት ለወባ በሽታ ተጋላጭ እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት የጸረ ወባ ትንኝ ማጥፊያ ኬሚካል አለመረጨቱንም አንስተዋል። ለሁሉም ማኅበረሰብ አጎበር ተደራሽ እንዳልኾነም አስገንዝበዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዮሴፍ ጉርባ አካባቢው ሞቃታማ በመኾኑ የተለያዩ ወረርሽኞች እና በሽታዎች በብዛት የሚከሰቱበት ነው ብለዋል።
በዞኑ “በአዲሱ በጀት ዓመት ከ56 ሺህ 800 በላይ ማኅበረሰቦች በወባ በሽታ ታመው መታከማቸውን ተናግረዋል። ይህም ከባለፈው ዓመት የሕሙማን ቁጥር አንጻር አብላጫ አለው ነው ያሉት። ይሁንና በወባ በሽታ አንድም ሰው አለመሞቱን ገልጸዋል።
የወባ መራቢያ ቦታዎችን ልየታ በማድረግ ከ656 ሺህ 200 ካሬ ሜትር በላይ የታቆሩ ውኃዎችን የማፋሰስ፣ ደረቅ ቆሻሻዎችኝ የማቃጠል፣ ለማፋሰስ የሚያስቸግሩ የታቆሩ ውኃማ ቦታዎችን ኬሚካል በመርጨት እና በማጨድ ወባን የመቆጣጠር እና የመከላከል ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ከክልል ጤና ቢሮ የተሰጠውን 25 ሺህ አጎበር ለማኅበረሰቡ እንደተሠራጨ ተናግረዋል። አጎበሩ ሙሉ በሙሉ ለማኅበረሰቡ አለመድረሱንም አንስተዋል። ቀጣይ ላልደረሱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ከክልል ጤና ቢሮ ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።
በገጠሩ አካባቢ ወባን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በ29 ቀበሌዎች እና በሦስት ወረዳዎች የኬሚካል እርጭት ሥራዎች መሠራታቸውንም አብራርተዋል። ለማኅበረሰቡም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱንም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ የወባ ስሜቶች እና ምልክቶች ሲሰሙት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ መታከም እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የታዘዘላቸውን መድኃኒትም በአግባቡ መውሰድ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ኅብረተሰቡ ወባን ለመከላከል የተቀደደም አጎበር ቢሆን ሰፍቶ በመጠቀም እና የታቆረ ውኃን በማፋሰስ፣ በማዳፈን እና ቆሻሻዎችን በማቃጠል ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!