አረጋውያንን መንከባከብ ሀገርን መንከባከብ ነው።

1

ሰቆጣ፡ ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ የሚከበረው የአረጋውያን ቀን በሰቆጣ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

አቶ አድህና ያለው የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ከ1968 ዓ.ም ጀምረው ጡረታ እስከወጡበት 2010 ዓ.ም ድረስ ሀገር እና ሕዝባቸውን ከባለሙያነት እስከ ኀላፊነት ያገለገሉ አባት ናቸው። ባለፉት ዓመታትም ለደሞዝ ሳይኾን ለሕዝብ ጥቅም ያለኝን ጉልበት እና ጊዜ ሳልሰስት ሰጥቻለሁ ነው ያሉት። በዚህም ከክልል እስከ ፌዴራል ድረስ የተለያዩ ሽልማቶችን እንዳገኙ አንስተዋል።

ወጣቱ ትውልድም ሥራን ወዳድና በሥራው ቁርጠኛ መኾን እንደሚገባው መክረዋል።

አረጋውያን መጻሐፍት ናቸው፤ ቀርበን ልናነባቸው ይገባል ያሉት ደግሞ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ትበርህ ታደሰ ናቸው።

አረጋውያን የወጣቶችን እንክብካቤ እና ድጋፍ ይሻሉ ያሉት ኃላፊዋ ለዚኽም ሁላችን ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሹመት ጥላሁን ጉልበታቸው ሳይደክም ለሕዝብና ለሀገር የታገሉ፣ የሠሩ እና የደከሙ አረጋውያንን ለመደገፍ እና በአቅማቸው ልክ የሚሄድ የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

“የሀገር ሰላም እንዲጸና አረጋውያን የከፈሉት መስዋዕትነት ከፍተኛ ነው፤ ዛሬም እየጠፉ ያሉ መልካም እሴቶቻችን እንዲጎለብቱ አረጋውያን ኀላፊነት አለባቸው” ያሉት አቶ ሹመት ወጣቱም የአባቶችን ምክር ሊቀበል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፉን የአረጋውያን ቀን በማስመልከት በሴቭ ዘ ችልድረን አጋርነት ሰቆጣ ማዕከል ለሚገኘው የመቄዶንያ አረጋውያን መርጃ ማዕድ የማጋራት እና እውቅና የመስጠት መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና አመራር ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው። 
Next articleእየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ መከላከል ይገባል።