የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና አመራር ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው። 

2

ባሕር ዳር: መስከረም 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ)”ሴቷ ሰላምን ትምራ” ክልላዊ የሴቶች ፎረም በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

 

የትምራን በጎ አድራጎት ድርጅት ጊዜያዊ ሥራ አስኪያጅ ዮዲት ታመነ ትምራን መጋቢት 2012 ዓ.ም በሲቪክ ማኅበራት ኤጀንሲ የተመዘገበች ለትርፍ ያልተቋቋመች ሀገር በቀል ድርጅት ናት ብለዋል።

 

ትምራን በሀገሪቱ የፖለቲካ ምሕዳር ውስጥ ያለውን የጾታ እኩልነት ክፍተት ለማጥበብ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና በማንኛውም ሕዝባዊ አሥተዳደር እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሴቶችን ትርጉም ያለው ሁለንተናዊ ተሳትፎና አመራር ለማረጋገጥ ትሠራለች ነው ያሉት።

 

ትምራን ሴቶች በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች በተደነገገው መሠረት በማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሮች ውስጥ እኩል ተሳታፊና መሪ የመኾን መብታቸው እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ለማድረግ እየሠራች መኾኗንም ተናግረዋል።

 

ሴቷ ሰላምን ትምራ በሚለው ፕሮግራማችን ስር ትምራን ከኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢንተግሬትድ ዴቨሎፕመንት (ELiDA) እና አድቮኬሲ ሴንተር ፎር ዴሞክራሲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት (ACDD) ጋር በጥምረት (Consortium) በመሆን ከUK FCDO ባገኘችው የገንዘብ ድጋፍ “Women Count for Peace” የተባለ ፕሮጀክት እየተገበረች መኾኗንም አንስተዋል።

 

የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ፣ ውክልና እና ውሳኔ ሰጪነትን ማረጋገጥ ነው። ፕሮጄክቱ በአማራ፣ በትግራይ እና በኦሮምያ ክልሎች እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ትምራን በአማራ ክልል የሚሠራውን እያስተባበረች መኾኗን ገልጸዋል።

 

የዛሬው የሴቶች የሰላም መድረክ በሰላም ግንባታ ሂደቶች ውስጥ ሴቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እና የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲኖራቸው ለማስቻል፤ ግንዛቤን ለመፍጠር እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ማረጋገጥ ይችሉ ዘንድ በጎ ተፅዕኖ ለማሳደር ነው ብለዋል።

 

የሴቶች ሰላም እና ደኅንነት አጀንዳን እና የረቂቅ ሀገራዊ የድርጊት መርሐ ግብር እንዲፀድቅ፤ ፀድቆም ቶሎ ወደ ሥራ መግባት እንዲችል፤ የሴቶች የሰላም እና ደኅንነት አጀንዳ በክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ መኾን ለማስቻል ያለመ መኾኑንም ገልጸዋል።

 

የአማራ ክልል ከጦርነት እና ከግጭት እያገገመ ባለበት ወቅት የሚካሄድ መድረክ መኾኑንም ተናግረዋል። ሴቶችን በብዛት ተጋላጭና ተጎጂ ተደርገው የሚታዩትን እይታ መቀልበስ፣ እንደ መሪ፣ እንደ ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ውሳኔ ሰጪዎች አድርጎ ማስቀመጥ ለሀገራዊ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ነው ብለዋል።

 

መድረኩ ሰላማችን የጋራ ኃላፊነታችን መኾኑን እንድናስታውስ ያስችላል ነው ያሉት። ሴቶች ትክክለኛ ቦታቸውን የሚይዙበት፤ አመራራቸው ዕውቅና አግኝቶ ተቋማዊ መዋቅራዊ እና ማኅበረሰባዊ ድጋፍ የሚያገኙበት ሥርዓት ማምጣት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመድኃኒቶች ያለአግባብ ከተወሰዱ መርዝ ናቸው፡፡