መድኃኒቶች ያለአግባብ ከተወሰዱ መርዝ ናቸው፡፡

4

ባሕር ዳር: መስከረም 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎መድኃኒቶች የሰውን ልጅ ከተለያዩ በሽታዎች ይፈውሳሉ፡፡ ይሁንና መድኃኒቶች ያለአግባብ ከተወሰዱ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

 

ለመኾኑ የመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ምንድን ነው?

‎የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑት አቶ ዘመኑ ሞላ የሕክምና መድኃኒቶችን ከሐኪም ትዕዛዝ ውጭ ከመድኃኒት መደብሮች ገዝቶ የመጠቀም ልምድ እንዳላቸው ነግረውናል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ለፋርማሲ ባለሙያ የሚሰማቸውን የሕመም ምልክት በመናገር እንደኾነም አንስተዋል፡፡

 

በተለይም የተለመዱ አይነት የጤና ችግሮች እንደ ራስ ምታት፣ ወባ፣ ሳል እና ሌሎች በሽታዎችን ሊያክሙ የሚችሉ መድኃኒቶችን ከሐኪም ትዕዛዝ ውጭ ገዝተው እንደሚጠቀሙ ነው የገለጹልን፡፡

‎ከሐኪም ትዕዛዝ ውጭ መድኃኒት ገዝቶ መጠቀም ስላለው ተጓዳኝ ችግር ግንዛቤው እንደሌላቸውም አንስተውልናል። በቅርቡ ባለቤታቸው ላይ የተከሰተውን ችግርም አጋርተውናል፡፡ ባለቤታቸው ለጓደኛ የፊት ቆዳን ለማከም የታዘዘ የሚቀባ መድኃኒት ያሽለኛል በሚል ተጠቅመው ራስን እስከመሳት የሚያደርስ አደጋ እንደደረሰባቸው አስታውሰዋል፡፡

 

በኋላም በሕክምና ሲረጋገጥ አላርጂክ እንደኾነ ነው የገለጹልን፡፡ ቆዳ ላይም ጉዳት ማድረሱን አንስተዋል፡፡መድሃኒቶችን ከሐኪም ትዕዛዝ ውጭ መጠቀም ያለውን ጉዳት ተገንዝቤያለሁ ነው ያሉት፡፡

‎የፋርማሲ ባለሙያ የኾኑት ፈለቀ ከፍያለው በባሕር ዳር ከተማ የመድኃኒት ቤት ባለቤት ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያ መድኃኒቶች በሁለት ይከፈላሉ ብለውናል ባለሙያው፡፡ ያለሐኪም ማዘዣ እና በሐኪም ትዕዛዝ ብቻ የሚሸጡ የመድኃኒት አይነቶች ናቸው ብለዋል፡፡

 

ይሁን እንጅ መድኃኒቶች መገዛት እና መወሰድ ያለባቸው በሐኪም ትዕዛዝ መሠረት መኾን አለበት ነው ያሉት፡፡

‎አብዛኞቹ መድኃኒቶች ታካሚዎች ተመርምረው በሐኪም ትዕዛዝ ብቻ መወሰድ ያለባቸው እንደኾኑ ይገልጻሉ፡፡

‎ያለማዘዣ የሚሸጡ መድሃኒቶች አብዛኞቹ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች እንደኾኑ ነው የገለጹልን። ሌሎች ጸረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ግን ያለሐኪም ትዕዛዝ ገዝቶ መውሰድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ነው ያሉት፡፡

 

ባላቸው ልምድ አብዛኛው ሰው ባለበት የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ሕመም ሲሰማ በጤና ተቋማት ተመርምረው ከመታከም ይልቅ ለፋርማሲ ባለሙያው የሚሰማቸውን የሕመም ስሜት ተናግረው መድኃኒት ገዝቶ የመጠቀም ልምድ አለ ብለዋል፡፡

‎ወደ ጤና ተቋማት በመሔድ ለመመርመር ያለውን የገንዘብ ወጭ ለመቀነስ እና በመድኃኒት ሽያጭ ላይ ያለው ቁጥጥር የላላ መኾን ለችግሩ እንደ ምክንያት መኾኑን አንስተዋል፡፡ መድኃኒቶች በአግባቡ ካልተወሰዱ ከማዳን ይልቅ የጤና ችግር ይፈጥራሉ ብለዋል፡፡

‎ሁሉም መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው፤ በአግባቡ ተወስደውም ጉዳት የሚያደርሱም አሉ ነው ያሉት። ይሁን እንጅ ሁሉም ሰው መድኃኒት ሲወስድ የሕክምና ምርመራ አድርጎ በሐኪም ትዕዛዝ መሠረት ሊኾን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

 

ኅብረተሰቡ መድኃኒቶችን ከመጠቀሙ በፊት ያላቸውን ተጓዳኝ ችግሮች አውቆ መጠቀም አለበት ነው ያሉት፡፡ ባለሙያዎችም የመድኃኒቶችን አወሳሰድ እና ተጓዳኝ ችግሮች በአግባቡ ለተጠቃሚዎች ማስረዳት እንደሚገባ ነው የገለጹልን፡፡

“‎መድኃኒቶች በአግባቡ ካልተወሰዱ መርዝ ናቸው” ያሉት ባለሙያው ኅብረተሰቡ መድኃኒቶችን ተመርምረው፣ በሐኪም ትዕዛዝ ብቻ እና በታዘዘው መሰረት ለታዘዘለት ሰው ብቻ መጠቀም እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

‎የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ስፔሻሊስት ዶክተር መኮንን አይችሉህም መድኃኒት ማለት ሕመሞችን ለመፈወስ፣ ለመከላከል እና ለምርምር የሚያገለግሉ ሥራዎችን ለመሥራት በሳይንሳዊ መንገድ የተቀመሙ ኬሚካል ናቸው ብለዋል፡፡

‎መድኃኒቶች ጠቃሚም፣ ጎጅም ባሕሪ አላቸው፡፡ ጠቀሜታቸው ለምርመር፣ በሽታዎችን ለመከላከል እንደ ክትባት እና በሽታዎችን በቀጥታ ለመፈወስ ነው ብለዋል፡፡ ይህ የሚኾነው በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውሉ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡

 

በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋሉ ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ለሕመም ከመዳረግ እስከ ሞት ድረስ የሚደርስ ጉዳት ያስከትላሉ ነው ያሉት፡፡

መድኃኒቶች ሕመምን ለመፈወስ በሚወሰዱበት ጊዜ ቀላል ችግሮች ሊኖሯቸው ይችላል ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት መድኃኒቶች ጠቃሚ መርዞች ናቸው ሊባል ሁሉ ይችላል ነው ያሉት፡፡

 

‎‎መድኃኒቶች ፈዋሽነታቸው ሊረጋገጥ በሚችልበት እና ከሐኪም ትዕዛዝ ይልቅ በዘፈቀደ ገዝቶ መጠቀም በሰው ሕይወት ላይ የሚያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ብለዋል ዶክተሩ፡፡

 

ጉዳቱም በአጭር ጊዜ መድኃኒት ወስዶ ከበሽታ አለመፈወስን እና በረጅም ጊዜ አካባቢን መበከል፣ እስከ ካንሰር እና ሞት ሊያደርስ ይችላል ነው ያሉት፡፡

‎‎በተለይ የጸረ ተሕዋስያን መድኃኒቶች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ሲወሰዱ በሽታን በመቋቋም መዳን በሚችሉ በሽታዎች ሰዎችን ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አንድን በሽታ ለማዳን ተብሎ በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይ እንደ ጉበት እና ኩላሊት ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚያስከትሉም ጠቁመዋል፡፡

‎የፋርማሲ ባለሙያዎች ሙያቸውን አክብረው ያለሐኪም ትዕዛዝ የማይወሰዱ መድሐኒቶችን መሸጥ የለባቸውም ነው ያሉት፡፡

 

‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ17 ሺህ በላይ ሕጻናትን በክትባቱ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የሞጣ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ። 
Next articleየሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና አመራር ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው።