ኅብረተሰቡ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የኾኑ አካባቢዎችን በማጽዳት ርብርብ እንዲያደርግ ተጠየቀ።

3

ፍኖተ ሰላም: መስከረም 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ስንሻው ፍሬው በጃቢጠህናን ወረዳ ዘጓይ ቀበሌ ነዋሪ ሲኾኑ ሰውነታቸውን የብርድ እና ማንቀጥቀጥ ስሜት ተሰምቷቸው በፍኖተሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ለሕክምና መጥተው ነው አሚኮ ያገኛቸው።

 

በጤና ጣቢያው ምርመራ ተደርጎላቸው በወባ በሽታ መያዛቸውን ነግረውናል። አካባቢው ውኃ የሚያቁር ቦታ በመኾኑ ከዚህ በፊት በወባ በሽታ ይታመሙ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህም እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ በመተኛት የግብርና ሥራዎችን ለማከናወን እንቅፋት መፍጠሩን ነው የተናገሩት።

 

በእርሳቸው ቤት ዙሪያ ብቻ ያሉ የወባ ትንኝ መራቢያ የሚኾኑ ስፍራዎችን ማጽዳት ቢችሉም በሽታውን መግታት ግን አለመቻላቸውን ነው የጠቆሙት። በመኾኑም መንግሥት እንደከዚህ በፊቱ አጎበር እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

 

ሌላው የዚህ ወረዳ የሆዳንሽ ጋታጎን ነዋሪው ወጣት መላኩ ሞሴ በፍኖተሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የአምስት ዓመት ሕጻን ልጁ በወባ በሽታ ታሞበት ሲያሳክም አግኝተነዋል። ሕጻኑ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ይታመም እንደነበርም ነግሮናል።

 

ከዚህ በፊት አካባቢው ለወባ ትንኝ መራቢያ አመች በመኾኑ የመከላከያ ኬሚካል ርጭት ይከናወን ስለነበር ስርጭቱ ቀንሶ እንደነበር አውስተዋል። አሁን ግን ርጭቱ በመቋረጡ ስርጭቱ እንዳይባባስ ስጋት ፈጥሯል ብለዋል።

 

በፍኖተሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ውስጥ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ተጠሪ እና የታካሚዎች ልየታ ክፍል ባለሙያ ፈንታሁን ታደለ ባለፉት ሦሥት ወራት በጤና ጣቢያው 4 ሺህ 461 ለሚኾኑ ሰዎች ምርመራ ተደርጎ 652 ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ተናግረዋል።

 

ለታማሚዎችም አስፈላጊው ሕክምና መሰጠቱን ገልጸዋል። ስርጭቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር መሻሻል አለው ብለዋል። ለኅብረተሰቡ ከሕክምና ባሻገር አስፈላጊ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሰጠ ነው ብለዋል።

 

በምዕራብ ጎጃም ዞን ባለፈው ዓመት 188 ሺህ 460 ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘው እንደንደነበር የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ኤፍሬም ክፍሌ ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥም ከ26 ሺህ በላይ የሚኾኑት ህፃናት እንደነበሩ አስታውሰዋል። ባለፈው ዓመት የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት አለመደረጉ እና የአጎበር ስርጭት አለመካሄዱ በሽታው እንዲስፋፋ ዕድል መፍጠሩን ነው የጠቆሙት።

 

በዚህ ዓመት ግን ስርጭቱን ለመግታት የተለያዩ የቅድመ መከላከል ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል። የወባ በሽታ በስፋት የሚስተዋልባቸው ወረዳዎችን በመለየት በሁለት ወረዳዎች ከ136 ሺህ በላይ አጎበር ለማኅበረሰቡ ተሰራጭቷል ብለዋል። በአንድ ወረዳ ደግሞ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ተከናውኗል።

 

በሁሉም የጤና ተቋማት በሽታውን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።

 

ከፍተኛ ስርጭት የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች በመለየት የቤት ለቤት ምርመራ እና ሕክምና ለመስጠትም እየተሠራ ነው ብለዋል።

 

ወረርሽኙ በሁሉም ወረዳዎች ተከስቷል፣ ስርጭቱ የበለጠ እንዳይስፋፋ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

 

በዚህ ዓመት እስካሁንም በዞኑ ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ መታመማቸውን እና ሕክምና መሰጠቱንም አስረድተዋል።

 

ኅብረተሰቡ የወባ ስርጭቱን እና የበሽታውን አስከፊነት በመረዳት ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የኾኑ አካባቢዎችን በማጽዳት ርብርብ እንዲያደርግም መምሪያ ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለሁሉም ምቹ የኾነች ኢትዮጵያን ለማየት በቅንጅት መሥራት ይገባል” 
Next articleከ17 ሺህ በላይ ሕጻናትን በክትባቱ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የሞጣ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።