የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ተደራሽነት ብቁ እና ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር ድርሻቸው የጎላ ነው።

4

ባሕር ዳር: መስከረም 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሦሥተኛ ዙር የተቀናጀ ክልላዊ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያም የክትባት ዘመቻ የማስጀመሪያ መርሐ ግብሩን በሰላም አርጊው ማርያም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የሃይማኖት አባቶች ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የደብረጽዮን ሰላምአርጊው ቤተ ክርስቲያን አሥተዳዳሪ እና የትምህርት ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢ መላከ ጽዮን ቆሞስ አባ ገብረ ሚካኤል የማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ በትምህርት ቤቱ በመከናወኑ ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ልጆችን ማስከተብ ጤናማ ትውልድ እንዲኖር ስለሚያደርግ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የልጆች ጤናማ አለመኾን ልጆችንም ወላጆችንም አንገት ያስደፋል፤ ልጆች ጤናማ ኾነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉም ማስከተብ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ወላጆች በተቀመጠው ጊዜ በትምህርት ቤት እና በየቤቱ የጤና ባለሙያዎች ሲንቀሳቀሱ ሁሉም መከተብ ያለባቸው ልጆችን በማስከተብ እንዲተባበሩ ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሙሐመድ ሁሴን በእስልምና ነፍሳችሁን ወደጥፋት መንገድ እና ሕይወታችሁ ላይ አደጋ ወደሚፈጥር መንገድ አትጣሉ የሚል አስተምህሮ አለ ብለዋል፡፡

የፖሊዮ በሽታ ሕጻናትን የሚጎዳ እና ከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚያስከትል በመኾኑ ማኅበረሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ከ10 ዓመት በታች የኾኑ ልጆችን እንዲያስከተብ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች እና በቤት ለቤት ክትባቱ ሲሰጥ ለጤና ባለሙያዎች ትብብር እንዲያደርጉም አደራ ብለዋል፡፡

የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን ኅብረት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ገብሬ አሰፋ ጤንነትን መጠበቅ፣ ጤናማ ልጆች እና ጤናማ ማኅበረሰብ መኖር አስፈላጊ በመኾኑ የልጆችን ጤንነት መጠበቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

አሁን የሚሰጠው ክትባት የልጆችን ጤና የሚጠብቅ በመኾኑ ወላጆች አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ክትባቱን ለሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ሁሉም አካል መተባበር እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ዓለም አሰፋ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ተደራሽነት ብቁ እና ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር ድርሻቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ዛሬ የጀመረው ዘመቻ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች ለኾኑ በከተማው ለሚኖሩ ለሁሉም ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት ይሰጣል ነው ያሉት፡፡

ክትባቱ የሚሰጠው በአጎራባች ዞኖች በሽታው በመገኘቱ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ከተማ አሥተዳደር ከ144ሺህ በላይ ሕጻናትን ለማስከተብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የሕጻናት ጉዳይ የሁሉንም ማኅበረሰብ ድርሻ እና ርብርብ የሚጠይቅ በመኾኑ ሁሉም ለክትባቱ መሳካት እንዲተባበር ጠይቀዋል፡፡

ክትባቱ በጤና ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና ቤት ለቤት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡ ለውጤታማነቱ ሁሉም አካል በኀላፊነት በመተባበር ሕጻናት እንዲከተቡ ማድረግ ይገባዋልም ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር አብርሃም አምሳል የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው በክልሉ በሚገኙ በአራት ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች በጥቅሉ በ58 ወረዳዎች ተጀምሯል ብለዋል፡፡

ሁሉም ክትባቱ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ በክልሉ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ይከተባሉ ተብሎ ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡

ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የኾኑ ሁሉም ሕጻናት ከዚህ በፊት ቢከተቡም ባይከተቡም መከተብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ለክትባቱ መሳካት ወላጆች፣ አሳዳጊዎች እና ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የተገነቡ የሞዴል የገጠር መንደሮች አስረከቡ። 
Next article“ለሁሉም ምቹ የኾነች ኢትዮጵያን ለማየት በቅንጅት መሥራት ይገባል”