
ባሕር ዳር: መስከረም 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ዋና ዋና የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች እና ሥጋቶች ተብለው ከተለዩ በሽታዎች ውስጥ ፖሊዮ ወይንም የልጅነት ልምሻ አንዱ ነው።
ፖሊዮ በዐይን በማይታይ የፖሊዮ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ በሽታ እንደኾነ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ባለሙያ የሺወርቅ አሞኜ ገልጸዋል። በዐይነ ምድር በተበከለ ምግብ ወይም ውኃ ከበሽተኛ ሰው ወደ ጤነኛ ሰው ይተላለፋል። በሽታው የነርቭ ሥርዓትን በማጥቃት የእጅ፣ የእግር ወይም የሁለቱም መዛል፣ መዘለፍለፍ፣ ዘላቂ የኾነ ሽባነት እና ሞትን ያስከትላል።
አብዛኛዎቹ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ምንም አይነት ምልክት አያሳዩም፤ አንዳንዴ ደግሞ በጣም ቀላል ምልከቶችን ሊያሳዩ ይችላሉ። በፖሊዮ በሽታ የጡንቻ መዛል ያጋጠመው ሰው የመዳን ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው። እስከ አሁንም መድኃኒት አልተገኘለትም።
➽. የፖሊዮ በሽታ ሥርጭት
በአማራ ከልል ከ2012 እስከ 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ 12 የፖሊዮ ሕሙማን ሪፖርት መደረጉን ባለሙያዋ ገልጸዋል።
በሽታውን ለመከላከል የወረርሽኝ ምላሽ ከትባት ዘመቻ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች፣ አጎራባች በኾኑ ዞኖች እና ወረዳዎች በዘመቻ እና በመደበኛ የከትባት መርሐ ግብር የማጠናከረ ሥራ መሠራቱን ነው የገለጹት። የፖሊዮ በሽታ ቅኝት ሥራም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ስምንት ወራት ደግሞ በኢትዮጵያ በ6 ክልሎች የፖሊዮ ወረርሽኝ መከሰቱን አንስተዋል፤ 40 የሚኾኑ ሕጻናትም በበሽታው ተጠቅተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ በአማራ ክልል የተከሰቱ ናቸው። በቅርቡ ለአፋር ክልል አጎረባች በኾኑ የጂቡቲ አንዳንድ ቦታዎች ጭምር የፖሊዮ ወረርሽኞች ሪፖርት መደረጉን ነው የገለጹት።
የተከሰተውን የፖሊዮ ወረርሽኝ በፍጥነት መቆጣጠር ካልተቻለ ወደ ሌሎችም አካባቢዎች በመዛመት በርካታ ልጆችን ለአካል ጉዳተኝነት እና ሞትም ሊዳርግ እንደሚችል ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ያልተከተቡ ብዙ ሕጻናት በተለያዩ አካባቢዎች መኖራቸው ለፖሊዮ ቫይረስ መዛመት እንደምክንያት አንስተዋል።
አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሕጻን መኖር ከ200 በላይ የሚኾኑ ሕጻናትን ለቫይረሱ ተጋላጭ ሊያደርጋቸው ይችላል ይላሉ።
➽. የፖሊዮ በሽታን እንዴት መከላከል ይቻላል?
የፖሊዮ ከትባት ደኅንነቱ የተጠበቀ መኾን አንዱ የበሽታ መከላከያ ዘዴ እንደኾነ ነው ባለሙያዋ የገለጹት። ፖሊዮን ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ1972 ጀምሮ ክትባት ሲሰጥ ቆይቷል።
አሁን ላይም በዓለም አቀፍ ደረጃም ኾነ እንደ ሀገር በሽታውን ለማጥፋት መደበኛ የፖሊዮ ክትባት ሽፋንን ከ90 በመቶ በላይ ማድረስ፣ ተጨማሪ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻዎችን ማካሄድ እና የበሽታዎች ቅኝት እና አሰሳ ሥራዎችን የማጠናከር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በቅርቡም በሁለት ዙሮች በዘመቻ መልክም ክትባቱ ተሠጥቷል። ሦሥተኛው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ደግሞ ከመስከረም 30/2018 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አራት ቀናት የሚሠጥ ይኾናል።
በአማራ ክልል እድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የኾኑ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት በክትባት ዘመቻው ተደራሽ ይሆናሉ።
ሰሜን ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ጎንደር ከተማ፣ ደብረ ታቦር ከተማ፣ ደብረ ማርቆስ ከተማ፣ ባሕር ዳር ከተማ ክትባቱ በዘመቻ የሚሠጥባቸው ናቸው።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!