
ደብረ ብርሃን፡ መስከረም 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ ለ25 ቀናት ሲሰጥ የነበረው የመጀመሪያው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የቆጣሪዎች ሥልጠና ተጠናቅቋል፡፡ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስጦታው መኮንን ቆጠራዉ በጥቅምት ወር መጀመሪያ እንደሚጀመር ገልጸዋል። ቆጣሪዎቹ በሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳዎችና በደብረብርሃን ከተማ ይሰማራሉ ብለዋል፡፡
ለዚህም ከሥልጠና ባሻገር የግብዓት አቀርቦት ሥራ ሲሠራ መቆቱን ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የሚገኙ መረጃዎች በዘርፉ ለሚዘጋጁ እቅዶች፣ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ትክክለኛ ግብዓት ኾነው ያገለግላሉ ነው ያሉት። በቆጠራው በመላው ሀገሪቷ የሚገኙ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ኢንተርፕራይዞች እንደሚካተቱ ተናግረዋል።
ሁሉም ዜጎችና የንግዱ ማኅበረሰብ የሚሰበሰበው መረጃ ለሀገር የሚጠቅም መኾኑን ተረድቶ መረጃውን በመስጠትና በጎ ትብብር በማድረግ እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግዛቸው ለገሰ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ለሀገር ያለው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ገልጸዋል። የዞን አሥተዳደሩ ለመረጃ አሰባሰቡ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እገዛ ያደርጋልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!