በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት የፍርድ ቤቶች ሚና በሚል ርዕስ ለአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ስልጠና ተሰጠ።

3
ባሕር ዳር: መስከረም 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለክልሉ ዳኞች ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ስልጠናዎች ላለፉት 10 ቀናት በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ሲሰጡ ቆይተዋል።
የተሰጡ ስልጠናዎች የዳኞችን በጥራት እና በብቃት የመወሰን አቅም የሚፈጥሩ ፣ እንዲሁም ዳኞች ነገሮችን ከብዙ አቅጣጫ ማየት እንዲችሉ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው።
ባለፉት አስር ቀናት፣ በርካታ ባለሙያዎች ከተለያዩ የትምህርት ፣ የሙያ እና የህይወት ልምድ ያካበቱትን እውቀት ለክልሉ ዳኞች ጉባኤ ተሳታፊዎች አቅርበዋል።
ተሳታፊዎች ከተከታተሏቸው ገለጻዎች መካከል በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት የዳኝነት ስርዓቱ ሚና በሚል ርዕስ የቀረበው አንዱ ሲሆን፣ አቅራቢው ደግሞ በአሜሪካን ሀገር ለ28 አመታት በዳኝነት እና በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሰሩት ደረጀ ደምሴ (ዶ.ር) ነበሩ።
አሜሪካን የዳበረ የዴሞክራሲ ባለቤት ያደረጋት ነጻ፣ ገለልተኛ እና ጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት በመዘርጋቷ መሆኑን ገልጸው፣ ገለልተኛ የዳኝነት ሥርዓት ለሀገር ሰላም ፣ ለዴሞክራሲ ግንባታ እና ለምጣኔ ሀብት እድገት አይነተኛ ሚና እንደሚጫዎት የሀገራትን ተሞክሮዎች እያነሱ አስረድተዋል።
የፍርድ ቤቶች ተቀዳሚ ሥራ በግለሰቦች፣ በማህበረሰብ፣ በንግድ ተቋማት እና በመንግሥታት መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን ማርገብ፣ ችግሮችን መፍታት እና ሰላምን መፍጠር መሆኑን ዶክተር ደረጀ በበይነ መረብ አማካኝነት ለተሳታፊዎች ባደረጉት ገለጻ አብራርተዋል።
ኅብረተሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት ባጣ ቁጥር የራሱን አማራጭ መውሰድ ይጀምራል ያሉት ዶክተር ደረጀ፣ ጉዳዩ ውሎ ሲያድር ለዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ ለሀገር ሰላም ጠንቅ መሆኑን አስቀድሞ በመረዳት፣ ጠንካራ ፍርድ ቤቶችን በመገንባቱ ሂደት ሁሉም የራሱን ድርሻ መውጣት እንዳለበት አብራርተዋል።
ዳኞች፣ በሕግ እና በማስረጃ ታግዘው ሁሌም አስተማሪ ውሳኔዎችን ማሳለፍ አለባቸው ያሉት ዶክተር ደረጀ ፣ ተጨማሪ ጥፋቶች እንዳይፈጸሙ፣ ተመሳሳይ ችግር ላይ የነበሩ ተጎጂዎችም ወደ ፍርድ ቤት መጠው ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግም በፍርድ ቤቶች የተወሰኑ ውሳኔዎችን በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች በማሰራጨት ማስተማሪያ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የግለሰቦችን ደህንነት ማስጠበቅ ፣ የሀገርን ደህንነት ማስጠበቅ ነው ያሉት ዶክተር ደረጀ፣ ዳኞች የግለሰቦችን መብት በእኩልነት ሊያስጠብቁ ይገባል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በ2017 ከ13 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች በሀገራችን ላይ ተሞክረዋል”
Next articleየልማት እቅድ እውን እንዲኾን ሰላምን ማጽናት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ።